ዜና፡ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከ ፊታችን መስከረም 30 ጀምሮ በሁለት ዙር በዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል፤ የቦታ ለውጡ ተፈታኞችን ሀሳብ ውስጥ ከቷል



ምስል- የትምህርት ሚኒስቴር ምኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9/ 2014 ዓ.ም፡- የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከመስከረም 30 /2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ዙር እንዲሰጥ መታቀዱን የትምህርት ሚኒስቴር  አስታወቋል፡፡ ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ዩኒቨርስቲዎች  ምንም አይነት የመደበኛ ተማሪ በግቢ እንዳይኖር እንዲያደርጉ፤  በቀጣይ በሚገለጸው ተማሪ ቁጥር ልክ ምግብ ለማቅረብ ዝግጅት እንዲያደርጉ፤ ለፈተናዎች ማቆያ ቦታ አንዲዘጋጅ እና  የፈተናውን አሰጣጥና ደህንነት የሚቆጣጠር በፕሬዚዳንት የሚመራ ዋና ግብረ-ኃይልና በየካምፓሶቹ በዲን /ካምፓስ ኃላፊ የሚመራ ንዑስ ግብረ-ኃይል እንዲያደራጁ መልዕክት ተላልፎላቸዋል ተብሏል። 

ዩኒቨርሲቲዎች የ2015ን የአካዳሚክ ካላንደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ወቅት (ከመስከረም 28 – ጥቅምት 17) ታሳቢ በማድረግ እንዲያዘጋጁ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ አሳስበዋል።          

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኦንላይን መስጠት እስከሚጀመር ድረስ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ የተወሰነው የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት ታስቦ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በስራና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀው በርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልፀዋል።

እነዚህ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች  በአቅራቢያቸው ወዳሉ ዩኒቨርስቲዎች አምርተው የሚፈተኑ ሲሆን የሚፈተኑት ዩንቨርስቲዎች ምግብ እና ማደሪያ ያዘጋጃሉ ተብሏል፡፡ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ” የክልል ባለሟሎች፣ የክልል ኃላፊዎችን ከፈተና ጉዳይ ጋር በመለየት ፤ ፈተናው እራሱ የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስለሆነ በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ብቻ እንስጥ እና  ተማሪዎቹን አጓጉዘን ቢቻል ሁሉንም ከክልላቸው ውጭ በሆኑ ክልሎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና የፌዴራል ተቋማት ውስጥ ለመስጠት  እየተዘጋጀን ነው” ብለዋል። ይህም የሆነው በሁለት ምክኒያት ነው ያሉት ፕ/ሩ አንደኛ በመንገድ ላይ ሊኖር የሚችለውን የመሰረቅ አደጋ ይቀንሰዋል። ሁለተኛ ክፍል ውስጥ ከተገባ በኃላ ለመስረቅ የሚቻልበትን አደጋ ይቀንሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።  

ከዚህ በፊት በ4 ኮድ (4 የተለያዩ ፈተናዎች/በጥያቄ አቀማመጥ) ሰሰጥ መቆየቱ ይሚታወስ ሲሆን ፤ የ2014 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን በ12 ኮድ (በጥያቄ አቀማመጥ ስብጥር) ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የጠቀሱት፡፡ ይህም የሆነው የፈተና ኩረጃን ለመከላከል ከሚሰሩት ስራዎች መካከል አንዱ መሆኑንና ጎን ለጎን ያሉ ተማሪዎች እርስ በእርስ የሚፈተኑት ፈተና የጥያቄው ዝርዝር (order) በፍፁም የተገናኘ እንዳይሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ለአዲስ ስታንዳርድ ሃሳቡን ያካፈለው የ12ኛ ክፍል ተፈታኙ አዲስ ሰመረ ውሳኔው የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ታስቦ መሆኑ መልካም ሆኖ ሳለ ፈተናዉን ቤተሰብ ጋረ ሆኖ መፈተን የተሻለ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በተለይ ለሴቶች የፈታናውን ወቅት ከቤተሰብ ጋር ሆነው ቢፈተኑ ነው ፈተናው ላይ ትኩረት አድርገው መፈተን የሚችሉት ሲል ገልጧል፡፡

ቅድስት (በመጀመሪያ ስሟ ብቻ መጠራት የፈለገች) የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በአዲስ አከባቢ ሄዳ መፈተኗ ለቤተሰቧ ስጋት እንደሆነ ገልፃ ይህ መልቀቂያ ፈተና በተማሪው ህይወት ላይ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ቢፈተኑ በራስ መተማመንናቸው እንደሚጨምር ተናግራለች፡፡

አስማረ ተሰማ እህቱ የሁለተኛ ደረጃ ተፈታኝ  ስትሆን በሃገሪቷ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር የተነሳ እህቴን ወደ ሌላ ክልል ለመላክ ስጋት ውስጥ ገብቻለው ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ክልል የፀጥታ ሁኔታ አስጊ በመሆኑ ተማሪዎቹ ከስጋት ነፃ ሆነው መፈተን ሊከብዳቸው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አክለዋል፡፡

ወላጆቹና ተማሪዎቹ ትምህርት ሚኒስቴር ተግባራዊ የሚደርገው አዲስ አሰራር አላማው የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት መሆኑ ተገቢ መሆኑን ገልፀው ወደ ሌላ ክልል ማስማራቱ ግን ቢቀር የተሻለ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.