ዜና ትንታኔ፡ የ2005 የ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ከውላችን በላይ ለዘጠኝ አመት እየቆጠብን ባለበት ሁኔታ የቤት እጣ ውስጥ ሳንካተት ቀርተናል ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ



ምስል: አዲስ አበባ ቤቶች ልማት

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም፡- በ2005 የ20/80 ባለ ሶስት መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ከውላችን በላይ ለዘጠኝ አመታት አየቆጠብን ቢሆንም በ13ኛው ዙር እንዲሁም ባሁኑ የ14ኛ ዙር እጣ ውስጥ ሳንካተት ቀርተናል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡ በመመሪያው መሰረት ቤቶቹ በስድስት አመት ውስጥ ተጠናቀው በአግባቡ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ማስረከብ የነበረባቸው ቢሆንም ለዘጠኝ አመታት ቆጥበን እጣ ውስጥ አለመካተታችን ሳያንስ ቤት የለም ተብለናል ብለዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የ2005 የ20/80 ባለ ስስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ከመንግሥት ጋር ባደረግነው የውል ስምምነት መሰረት መንግሥት ቃል የገባውን አምነን መኖሪያ ቤት ይኖረናል በሚል ተስፋ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ ጋር እየታገልን ያለመታከት በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሠረት እስካሁን ድረስ 2 ቢሊየን ብር የቆጥብን ቢሆንም እጣ ውስጥ ሳንገባ ቀርተናል ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም አቤቱታና ቅሬታ ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቢሮ  በደብዳቤና በአካል ቀርበን አስረድተን በግልባጭም የከተማ አስተዳደሩን ከንቲባ፣ ም/ከንቲባንና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው 15 የመንግስት ተቋማት አቅርበናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ  “የከንቲባና ከንቲባ ጽ/ቤቶች የግልባጭ ቅሬታ ደብዳቤያችንን ሪፈረንሰ ቁጥርና ማህተብ የሌለው ደብዳቤ አንቀበልም ብለው መልሰውናል“ ብለዋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙባረክ ረሺድ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ወደ ቤት ማስተላለት ምክትል ኃላፊ አቶ አውራሪስ ከበደ መርቶን ኃላፊው ቅሬታ ማቅረብ እንደማንችልና ቤት እንደሌለ ነግረውን ዝም “ብላቹ ቆጥቡ” ብለውናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሰብሳቢው አክለውም በ13ኛው ዙር ከ5,400 በላይ የ2005 የ20/80 ባለሦስት መኝታ ተመዝጋቢዎች ቤት የተረከቡ ሲሆን የተቀረነው ተመዝጋቢ በ14ኛው ዙር እንደሚደርሰን ተነግሮን የነበር ቢሆንም እጣ ውስጥ ሳንካተት ቀርተናል ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ባለሶስት መኝታ ቤት እጣ ውስጥ ያልተካተተበትን ምክንያት በግልፅ ያሳውቀን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ሄለን ኤፍሬም እስካሁን ድረስ ቁጠባውን በንቃትና በብቃት ለ9 ተከታታይ ዓመታት እየቆጠበች እንደሆነ ገልፃ “በተዋዋልነው በ2005 ምዝገባ የቁጠባ ውል መሰረት ለ7 ተከታታይ ዓመታት ወይም የቤቱን 20 በመቶ የቆጠበ በቀጥታ ዕጣ ውስጥ እንደሚካተት ይገልጻል። ነገር ግን ለ9 ተከታታይ ዓመታት ስንቆጥብ ቆይተን እጣ ውስጥ ሳንካተት በመቅረታችን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ብንጠይቅም ምልስ ሚሰጠን አጥተናል” ስትል አስረድታለች፡፡

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሸገር ኤፍኤም በሰጡት ቃለ-ምልልስ የ1997 ዓ.ም ባለ ሶስት መኝታ ክፍል ቤት በመጠናቀቁ በቀጣይ ለ2005 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች ቤት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹ በ13ኛው ዙር የ2005 የ20/80 ተመዝጋቢዎች ከ5,400 በላይ ሰዎች ባለሦስት መኝታ ቤት የተረከቡ ሲሆን የተቀሩት በ13ኛው እና በቅርቡ በተሰረዘው የ14ኛው እጣ ውስጥም እንዳልተካተቱ ያስረዳሉ።

የከተማ መስተዳድሩ በያዝነው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በሰጠው መግለጫ በ1997 ተመዝጋቢዎች ውስጥ በ20/80 ባለሶስት መኝታ እጣ ሊወጣለት የሚችል ተመዝጋቢ የለም በሚል ቤቶቹን በሚያስተዳድረው ቦርድ ውሳኔ ፕሮግራሙ ከሲስተም ውጪ እንዲሆን መደረጉን ገልፆ በዚህም ምክንያት በ14ኛው ዙር እጣ ማስተናገድ ያልተቻለ ሲሆን ከተዘጋ በኋላ  ግን ከባንክ የተገኘው መረጃ ቁጠባ ያላቋረጡና ብቁ የሆኑ  በመገኘታቸው አስተዳደሩ እነኚህን ተመዝጋቢዎች ምንም እንኳን ፕሮግራሙ በይፋ የተዘጋ ቢሆንም ከባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት በአግባቡ እስከቆጠቡ ድረስ ማስተናገድ ስለሚገባ  የ1997 ተመዝጋቢ ለሆኑ ባለሶስት መኝታ ቤቶች በአግባቡ የቆጠቡ አስተዳደሩ በሚያወጣው ፕሮግራም በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ መሆኑን አሳውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች አገልግሎት ኃላፊዎችና የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት በተለያየ ጊዜ በሰጡዋቸው መግለጫዎችና ማብራሪያዎች በባለ 3 መኝታ ቤቶች ፕሮግራም የተሰራው ቤትና በአግባቡ የቆጠቡት ሲነጻጸሩ የቤቱ ቁጥር ከቆጣቢው ቁጥር የሚበልጥ መሆኑን በድምጽ፣ በምስልና በህትመት ሚዲያ የሰጧቸው መግለጫዎችና ማብራሪያዎች ተጠቃሽ ሀኖ ሳለ ቤት የለም መባል የለብንም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል።

ሀምሌ 01 ቀን  2014 ዓ.ም በወጣው የ14ኛው እጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የ20/80 ባለ 3 መኝታ ቤቶች አለመካተታቸው በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ወሃቢረቢ የገለፁ ሲሆን የባለ ሶስት መኝታ ቤት በተመለከተም ባለፈው ዙር ዋጋውን እስከ 1500 ብር ቁጠባ ድረስ በማውረድ በማስተናገድ የቤቶች ቦርድ ፕሮግራሙን መዝጋቱን አስታውሰው ፤በዚህ ዙር ለማስተናገድ አጠቃላይ ሲስተሙን የሚያዛባ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ እንደሚታ መግለፃቸውን አዲስ ስታንዳርደ ዘግባለች፡፡

የ20/80 የ14ኛ ዙር የ40/60 3ኛ ዙር የጋራ መኖርያ ቤት እጣ አውጣጥ ላይ የ20/80 ባለሶስት መኝታ የጋራ መኖርያ ቤት በእጣ ውስጥ አለመካተቱ አነጋገሪ ሆኖ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ይህንንም አስመልክቶ የከተማ መስተዳድሩ ባወጣው መግለጫ  በ14ኛው ዙር ለ20/80 የቤት ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ እጣ የወጣባቸውና የተስተናገዱት የ1997 ተመዛጋቢዎች ብቻ መሆናቸውን ገልፆ የ2005 የ20/80 ተመዝጋቢዎች ግን ከስቱዲዮ ጀምሮ ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ በሙሉ በእጣ ውስጥ አልተካተቱም ብሏል፡፡ መግለጫው የ40/60 የቤት ፕሮግራም ግን በ2005 ዓ.ም ብቁ የሆኑ ሙሉ ለሙሉ በእጣ ተካተው በዚህ ዙር የእጣ አወጣጥ በ40/60 ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ ቤቶች እጣ እንደወጣላቸውም አክሎ የገለፀ ሲሆን በዚህ ዙር ያልተስተናገዱት 1997 ዓ.ም የተመዘገቡ ባለሶስት መኝታ ተመዝጋቢዎች ብቻ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

ሀምሌ 01 ቀን  2014 ዓ.ም የወጣውን የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች  ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ተከትሎ በተደረገ የኦዲት ሥራ  በባንክ የተላከው እና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ያለው መሆኑንና ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች መከሰታቸውን ተከትሎ እጣው ሙሉ ለሙሉ መሰረዙን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ማስታወቁን አዲስ ስታንዳር ዘግባለች፡፡

ከንቲባ አዳነች 14 ኛዉን የ20/80 እንዲሁም 3ኛ ዙር የ40/60 የመኖሪያ ቤት እጣ የማዉጣት ፕሮግራም ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር፤ የአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የቤት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያወጣባቸውን ቤቶች የሚያስተዳድረው ቴክኖሎጂ ሲስተም ለተለያየ ህገወጥ ድርጊት እንዳይጋለጥ ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ የተሰራ መተግበርያ በመሆኑ ይህም አስተማማኝና ግልፅነት እንዲሁም ፍትሃዊ አሰራር የዘረጋ ነው ተብሎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ትክኖሎጂው የቅድሚያ ተጠቃሚነት አወሳሰንን በፍትሃዊነት የሚተገብርና ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት በእጣው ላይ በፍትሃዊነት አካቶ ሊያወጣ በሚችል መንገድ የተሰራ ነው ቢባልለትም  በተደረገ የኦዲት ሥራ  በባንክ የተላከው እና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ያለው በመሆኑ ሲስተሙን በመጠቀም አመራር የመራው የማጭበርበር ድርጊት መፈፀሙ ተገልጧል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.