ዜና፡ የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ



ምስል ፡ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም – ኢትዮጵያ 17ኛውን አለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ህዳር 2015 ዓ.ም. እንድታዘጋጅ መመረጧን ተከትሎ የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ “በይነ-መረብ ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአካል እና በኦንላይን ጭምር በተካሄደው በዚህ የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ “የበይነ-መረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው የበይነ-መረብ ተደራሽነት፣ የበይነ-መረብ ተደራሽነት እንደ መሰረታዊ መብት” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀጣይ አመት  ለምታካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፉ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ መሰረት የጣለ እና የተለያዩ ልምዶች የተገኝበት ነው ተብሏል።

መንግስትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትን ማለትም የግሉ ዘርፍ፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ መንግሰታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች፣ ወጣቶች ተሳታፊ ያረገው ጉባኤው በይነ-መረብን ለራስ ጥቅም ብቻ ለመቆጣጠር የሚያነሳሱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እና የጎንዮሽ ጉዳቶች ኢንተርኔት እየሰጠ ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ቀጣይነት አደጋ ውስጥ እንዳይከቱት እና አዳዲሰ ፍላጎቶች በሚገባ መስተናገድ እንዲችሉ በይነ መረብ በሁሉም ባለድርሻዎች የጋራ ጥበቃ ሊደርግለት እና እድገቱን አስተማማኝ የሚያደርግ የአሰራር ስርዓት ሊበጅለት አንደሚገባ ተገልጧል፡፡

በተጨማሪም እነዚህን ስጋቶች ለመቀነሰ እና የበይነመረብ እድገት እና አካታችነት በተገቢው መንገድ እንዲሄድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለበይነ መረብ አሰተዳደር ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው የተባለው።

የበይነመረብ ለብዙሃኑ የእድገት ምንጭነት በመሆን እየሰጠ ያለው አገልግሎት እንዳለ ሆኖ እስካሁን የበይነመረብ አገልግሎት የማያገኙ በርካቶች በመሆናቸው አገልግሎት ያልተዳረሳቸው በቢሊየን የሚቆጠሩ የማህብረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ሲሆኑ በይነመረብ የበለጠ ባለ ብዙ ባህል እና ቋንቋ እየሆነ የሚሄድ  በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቀበታል ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በአገራችን ከ25 ሚሊየን በላይ ሰወች   ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ገልፀው ባሁኑ  በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜ የግለሰቦች፣ የተቋማትና የሀገራት የቀን ተቀን እንቅስቃሴ በበይነ-መረብና ሌሎች የግኑኝነት ቻናሎች ላይ ጥገኛ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ ከጥገኝነት ባሻገር በበይነ-መረብና ሌሎች የግንኙነት መንገዶች አማካኝነት ከፍተኛ የሆነ አኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ለውጦች በሰዎች፣ ተቋማት እንዲሁም ሀገራት ከቀን ተቀን ዉሏቸው ላይ እየተካሄዱ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ “በይነ-መረብ የሚፈጥራቸው እድሎችና ጠቀሜታዎች እንዳሉ ሁሉ ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች አሉ፤ በተለይ ሀገራት የህግና የአሰራር ማእቀፍ ካላስቀመጡ ከሳይበር ጥቃት ከተዛባ መረጃ ስርጭትና ተያያዥ የሆኑ ፈተናዎች ያጋጥማቸዋል፡፡ እንደ ሀገር እነዚህን ፈተናዎች ለመቅረፍ እንዲሁም ዜጎችና ተጠቃሚዎች የሚያደረጉት ግኑንነቶች አስተማማኝ እንዲሆኑ የኢንፎረሜሽንና ኮሙኒከኬሽን ቴክኖሎጂ ልዩ ልዩ አዋጆች በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል፡፡ ለአብነት ያህልም  በስራ ላይ ከዋሉ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅና የኢትራንዛክሽን የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅን የማርቀቅ ሂደቱ ተጠናቆ ለውሳኔ ለመንግስት መቅረብ ላይ ይገናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.