ዜና ትንታኔ፡ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤትና ፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጨምሮ በስምነት የፌዴራል እና የክልል መንግስት ተቋማት ላይ ክስ አቀረቡ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24/2015 ዓ.ም፡- የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ከታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ የዎላይታ ብሄር የራሱን እድል በራሱ የመወሰንና ራሱን የማስተዳደር መብትን በመጠቀም በክልል የመዳራጀት ህግን በመከተል ያቀረበዉን የመብት ጥያቄ ተከትሎ በብሔሩ ግለሰብ አባላትና በቡድን እንዲሁም በብሔሩ ላይ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፈፅመዋል ባሏቸው አካላት ላይ ክስ አቀረቡ፡፡

ፓርቲዎቹ ክሱን ያቀረቡት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት( 1ኛ ተከሳሽ) ፣በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት( ጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት) (2ኛ ተከሳሽ)፣ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ( 3ኛ ተከሳሽ)፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መንግስት(የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት) (4ኛ ተከሳሽ) ፣በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ምክር ቤት( 5ኛ ተከሳሽ) ፣ በወላይታ ዞን አስተዳደር(6ኛ ተከሳሽ)፣በወላይታ ዞን ምክር ቤት(7ኛ ተከሳሽ) እና ብልጽግና ፓርቲ ( 8ኛ ተከሳሽ) ላይ ሲሆን ክሱን የመሰረቱት ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ስራ አስፈፃሚ አባልና የወላይታ ወጣቶች አደረጃጀት አመራር የሆኑት አቶ አሸናፊ ከበደ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ለተከሳሶቹ መጥሪያው እንደደረሳቸው ገልፀው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነት ችሎት ፍ/ብሄር ምድብ ክስ ችሎትለሀምሌ 3 የፅሁፍ መልስ እንዲሰጡና ለሀምሌ 7 ደግሞ ለቃል ክርክር ቀጠሮ ሰጥቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ከህዝብ ፍላጎትና ከሕግ አግባብ ውጭ በአንድ ፓርቲ እና በጥቂት ተሸዋሚዎች ፍላጎት፣ የህዝብ እጣፈንታ በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አሸናፊ ይህን ተግባር ደግሞ በሃይልና ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማስፈፀም የደቡብ ክልል እያደረገ ያለው ጥድፊያ አደጋ ያለው ነው ብለዋል፡፡

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ያቀረቡት ክስ ዝርዝር አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ የህዝብ ዉክልና ያለዉ የዎላይታ ዞን ምክር ቤት (7ኛ ተከሳሽ) ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 4ኛ ዙር 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔር ክልል የመሆን ጥያቄን በሙሉ ድምፅ ቢያፀድቅም ውሳኔውን 5ኛ ተከሳሽ  በክልሉ ህገ መንግስት እና በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 39(1)(3) እና 47/3/ለ በተደነገገዉ መሰረት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የዎላይታን ብሔር ለህዝበ ውሳኔ ሳያደራጅ በዝምታ በመቅረቱ ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽ በሕግ ብሔሩ የራሱን እድል በራሱ የመወሰንና በራሱ የማስተዳደር ያልተገደበ መብትን በተሟላ ሁኔታ እዉን እንዲያደርግ የተሰጠውን ግዴታ በህጉ በተጠቀሰው 2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ አለመስጠቱ ብሔሩ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39(1) እና(3) ያለገደብ የተረጋገጠለትን መብት መነፈጉ አስታውቋል፡፡

ከነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም ባሉት ቃናት ዉስጥ በሙሉ ዎላይታ ዞን ዉስጥ 4ኛ ተከሳሽ የሚያዘዉ የጸጥታ መዋቅር የደ/ብ/ብ/ህ/ክ ፓሊስ አባላትና ልዩ ኃይል እና 2ኛ ተከሳሽ የሚያዘዉ የፌዴራል ጸጥታ መዋቅር የሆኑት (የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላካያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፓሊስ) ተመጣጣኝ ባልሆነ እና ህግን ባልተከተለ የጦር መሳሪያ አጠቃቃም በተወሰደዉ እርምጃ ወይም ጥቃት 38 ሰዎች በላይ መገደላቸዉ እና ከ 200 በላይ ሰዎች ቀላልና ከባድ አካል ጉዳት ከመድረሱ በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የብሔሩ አባላት ለህገ ወጥ እስርና ያለፍርድ፤ ያለምንም ምርመራና የተያዙ ሰዎች መብት በሚጥስ መልኩ በማጎሪያ ካምፕ እንዲቆዩ ተደርገዋል ያለው ክሱ በግርጊቱም የመብት ጥሰት ስለመሆኑ በሰብአዊ ምርመራ ሪፖርቶች ተመላክቷል ብሏል፡፡

በመሆኑም ለተፈጸመዉ ልዩ ልዩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች 2ኛ፤4ኛ፤6ኛ እና 8ኛ መብቶቹን የማክበር፤ የመጠበቅና የሟሟላት ግዴታቸዉን አልተወጡም እንዲሁም መብት ጥሰቱ ከተከሰተ በኃላ እንኳን በተለያዩ እርከን ደረጃ ያሉት የተከሳሶች የስራ ኃላፊዎች ለሰዉ ህይወትና አካል ጉዳት የፈጸሙት፤ ያዘዙት፤ ስልጣን እያላቸዉ ያልጠበቁት፤ የእርምት እርምጃ ያልወሰዱት አካላት ላይ ምንም አይነት ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደም፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉትና የሟች ቤተሰቦች/ የሟች ጥገኞች ተገቢዉን ካሳ አላገኙም ሲሉ ፓርቲዎቹ በክሱ ላይ ገልፀዋል፡፡

ከአጎራባች ዞኖች ጋር በጋራ ከልል የመሆን ውሳኔ የሰጠው የ 7ኛ ተከሳሽ የምርጫ ዘመኑ ያበቃና በዞኑ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ዞኑን ለማስተዳደር በሕገ መንግስቱ መሰረት ስልጣን የሌለው መሆኑን የጠቀሰው ክሱ አክሎም የ1ኛ ተከሳሽ አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 19 እና ይህንን አዋጅ የተካው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀፅ 25 በግልፅ የጣሰ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በመሆኑም ከሳሾቹ 2ኛ፤4ኛ፤6ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች የዎላይታ ብሔር የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ተጠቅሞ ራሱን ለማስተዳደር የዎላይታ ብሔራዊ ክልል እንዲቋቋም አጽድቆ የህዝበ ዉሳኔ እንዲደራጅ የጠየቀዉን መብት በኃይል ለማፈን በማሰብ በሕይወት፤ በአካል ደህንነትና የነጻነት መብት፤ ኢሰብኣዊ በሆነዉ አያያዝ በመፈጸም፤ የተያዙ ሰዎችና የተከሰሱ ሰዎች ላይ የደረሰዉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት አለባቸዉ ተብሎ እንዲወሰንላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ የምርጫ ዘመኑ አልፏል ያሉት 7ኛ ተከሳሽ በጋራ እንዲደራጅ በማለት በ2ኛ ዙር ውሳኔ በማስጠት፤ 1ኛ ተከሳሽ  ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከአጎራባች ዞኖች ጋር በክላስተር በጋራ ክልል እንዲመሰረት ዉሳኔ በመስጠት፤ 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ ሰብአዊ መብትን የሚጥስ፣ህግንና ህገ መንግስትን ያልተከተለ ህዝበ ዉሳኔ በማስፈጸማቸዉ ለደረሰዉ የዎላይታ ብሔር ራሱ የማስተዳደር ሰብዓዊ መብት ጥሰት በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት አለባቸዉ ተብሎ እንዲወሰንላቸውም አክለው ጠይቀዋል

ሁሉም ተከሳሾች ለተፈጸመዉ ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እዉቅና እንዲሰጡና በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲወሰንም ፓርቲዎቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለተፈፀመባቸው፣ የዎላይታ ብሔር የራስን እድል በራስ የመወሰንና በራሱ ማስተዳደር መብት ጋር ተያይዞ በደረሰዉ ጉዳት መጠን ተጎጅዎች የሚገባቸውን ካሳ ተከሳሾቹ እንዲከፍሉ ይወሰንልን ብለዋል፡፡

አቶ አሸናፊ “እየተፈፀመ ያለው ጥሰት የአካባቢውን ሰላም፣ ልማትና ቀጣይ የህዝብ እጣተንታ እጅግ ሊፈታተን የሚችል በመሆኑ ሁሉም ከዚህ ተቆጥቦ ለሕግና ለሕገ-መንግስታዊነት ቦታ ሰጥቶ ህዝቦች የሚፈልጉትንና ቀላቂ ልማት ሊያስገኝ የሚችል ተግባሮች መከናወን አለባቸው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን ሕግ የያዘው በመሆኑ ቀጣዩን በጋራ የምናየው ይሆናልም ብለዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.