አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6 ፣ 2014 – በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጸሎትና ሌሎች ዝግጅቶች እንዳይደረጉ በመከልከላቸው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያቀረቡትን ቅሬታዎች በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጉዳዩ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በማገናኘት ሲሰራጭ በመቆየቱ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው ገለጿል ሚኒስቴሩ።
መግለጫው እንደዚህ ያሉ ቅሬታዎች የሀገሪቱን የፌደራል ስርዓት አሰራር በውል ካለመረዳት የመጣ መሆኑን በማስረዳት በፌደራል የትምህርት ሚኒስቴርና በክልሎች በሚተዳደሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሰራር የግንኙነት ማዕቀፍ መረዳት ለሚፈልጉ ወገኖች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ሚኒስቴሩ አዋጅ 1263/2014 አንቀጽ 34ን በመጥቀስ ጉዳዩ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች አቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር በክልል ትምህርት ቢሮዎች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ መገደቡን ገልጿል። ይህን ተከትሎም ከሰሞኑ ከሀይማኖታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተነሱ ቅሬታዎች በህገ መንግስቱ መሰረት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ትምህረት ቢሮን እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር አለመሆኑን ገልጿል፡፡
መግለጫው የብሄራዊ ፖሊሲ መርሆችና አላማዎች አንቀፅ 90 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት ትምህርት በማንኛውም መልኩ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካዊ እና ከባህላዊ ተጽእኖ የጸዳ መሆን አለበት የሚል የህገ-መንግስቱ አስገዳጅ ድንጋጌዎች ውስጥ ተካትቶ እንደሚገኝ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጋር በስልክ ባደረገው ውይይት በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች በፀሎት ሰአት ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ ፀሎት እንዲያደርጉ የትምህርት ቢሮ መወሰኑን ምክር ቤቱ እንዳረጋገጠ ይታወሳል።አስ