ዜና፡ አጣዬ ዲስትሪክት ሆስፒታል የእርዳታ ጥሪ አቀረበ

ጌታሁን ፀጋዬ 

.አዲስ አበባ ሚያዚያ 7፣ 2014፣ ፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የአጣዬ ወረዳ ሆስፒታል የላብራቶሪው ክፍል መስራት በማቆሙ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ ብዙ አየሁ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ላብራቶሪው  በመዘረፉ አሁን ስራ አቁሟል። በሆስፒታሉ ሲቢሲ (CBC) የደም መመርመሪያ ማሽን ሶስት ብቻ እንደነበር አስታውሰው ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ በትግራይ ሃይሎች ጦር ተዘርፈው እንደተወሰዱ እና የቀረው አንዱ ማሽን ደግሞ እነዚሁ ሃይሎች እንዳወደሙት ተናግረዋል። “የጤና ባለሙያዎች አካላዊ እና ቀለል ያሉ ህክምና በመስጠት ላይ የተወሰነ ነው” ያሉት ሃላፊው  “አሁን ታካሚዎቻችንን በአቅራቢያው ባሉ እንደ ሸዋ ሮቢት እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ላሉ ሆስፒታሎች መላክ ጀምረናል” ብለዋል።

ዶክተር ተሾመ ሆስፒታሉ በነበረው ጦርነት ክፉኛ እንደተጎዳ ተናግረው የጉዳቱም መጠን በግምት እስከ 54 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን አብራርተዋል። “ምንም እንኳን ህንጻውን መጠገን ብንችልም ህመምተኞችን ለማከም እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የህክምና ማሳሪያዎች መተካት አልቻልንም” ብለዋል ሃላፊው። 

ዶክተር ተሾመ አጣዬ ሆስፒታል ግምቱ ስድስት መቶ ሽህ ብር የሚያወጣ የህክምና እቃዎች ከስልጤ ዞን ወራቤ ሆስፒታል ያገኘው ብቸኛ እርዳታ መሆኑን ተናግረዋል። “ስለ እርዳታው እናመሰግናለን ነገር ግን ሆስፒታሉ እጅግ ከፍ ያለ እርዳታ ያስፈልገዋል” ብለዋል ሜዲካል ዳይሬክተሩ።

አጣዬ ሆስፒታል በበኩሉ የካቲት 3፣ 2014 ዓ.ም የታጠቁ ሃይሎች ሆስፒታሉ ላይ ጥቃት እንደፈፀሙ አሳውቋል። ደብዳቤው ሲቢሲ የደም መመርመሪያ ማሽን፣ የኬሚስትሪ ሪኤጀንት ማሽን፣ ኤልክትሮላይት ማሽን፣ እና የደም መርጋት ማሽን ለሆስፒታሉ እንደሚያስፈልጉት ጠቅሶ የሚመለከተው ማንኛውም አካል እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል። 

እንደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ላብራቶሪው  በቀን እስከ አምስት መቶ በሽተኞችን ያገለግል ነበር። “አሁን ላይ እነዚህ ሁሉ ህመምተኞች እዚሁ ከተማ መታከም ሲችሉ ወደ ሌሎች ከተሞች ለመታከም በሚል ለጉዞ እና  ላልተፈለገ ወጪ ተዳርገዋል” ያሉት ሃላፊው አክለውም “ሁሉም ታካሚዎች ይህንን ወጪ መሸፈን አይችሉም። እንደዚህ ሆነው ማየትም ያሳዝናል” ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.