ዜና:-ባይደን የኢትዮጵያን የአጎዋ ጥቅሞችን አቋረጡ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 15፣2014 ዓም፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገራትን ከአፍሪካ ግሮውዝ ኦፖርቹኒቲ አክት (አጎዋ) የቀረጥና ታሪፍ ነፃ መብት መሰረዛቸውን ይፋ አደረጉ፡፡

ኢትዮጵያ፣ ጊኒ እና ማሊ በአንቀጽ 506A(a)(1) የተገለጹትን የአጎዋ መስፈርቶች እንዳላሟሉ  በመጥቀስ ሶስቱን ከፊል የሰሃራ አፍሪካ ሃገራትን ከታህሳስ 23፣2014 ዓም ጀምሮ – ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንደሚታደዱ ፕሬዚዳንቱ አሳውቀዋል።።

ህዳር 12፤ 2014 ዓም  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ለማገድ  አሜሪካ ልትወስደው ያለችውን ውሳኔ በመቃወም “የተሳሳተ እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ለዜጎች ደህንነት ዋጋ ያልሰጠና  ቁርጠኝነትን  ከግምት ውስጥ ያላስገባ” በማለት ኮንኖታል።  ኢትዮጵያ ውሳኔውን በመቃወም  “በአብዛኛው ከ200,000 በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች  እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሴቶች ኑሮ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል” ስትል ተናግራለች።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ከታህሳስ 23፣2014 ዓም የአጎዋ ልዩ መብቶችን ለመሻር መወሰናቸውን ለአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ባሳወቁት ማግስት የኢትዮጵያ መንግስት የተቃወመ ሲሆን በወቅቱም ጆ ባይደን   “የኢትዮጵያ መንግስት የአጎዋ የተጠቃሚነት መስፈርቶችን ለማሟላት የሚያደርገውን መሻሻሎች እንገመግማለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ የዩኤስ ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን (ዲ-ኤም.ዲ.) እና የኮንግረስ አባል የሆኑት ኬረን ባስ (ዲ-ካሊፍ) ፕሬዝዳንቱ የአስተዳደሩን ውሳኔ እንደገና እንዲያጤኑት ቢጠይቁም ውሳኔው ተላልፏል። በጋረ ባወጡትም መግለጫ “በዚህ ግጭት በሁለቱም ወገኖች የተፈፀመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በፍፁም እያወገዝን፤ የአጎዋ ጥቅማጥቅሞች መታገድ ግን  ለጦርነቱ ምንም አይነት አስተዋጽኦ ያላደርጉ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ኢትዮጵያውያንን  ይጎዳል የሚል ስጋት አለን’’ በማለት ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪ እና የንግድ ተደራዳሪ ዋና አማካሪ ማሞ ምህረቱ ጋር ባደረጉት የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ በቂ ትኩረት ካልተሰጠው  ኢትዮጵያ የአጎዋ ልዩ መብቶችን የምታጣበት ሁኔታ እንዳለ ማሳሰባቸው ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.