ዜና: በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ መካከል እየተካሄደ ያለው የእርቅ ሂደት የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም : ኢሰመኮ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15/2014 – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል የአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት በክልሉ መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል እየተካሄደ የሚነኘው ሽምግልና በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ለተፈጸመው ግድያ የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም ሲል አሳስቧል። 

ኮሚሽኑ ከከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ጋር ተያይዞ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ክትትል አድርጌያለሁ ሲል ትላንት ባወጣው መግለጫ አሳወቋል፡፡ በክትትሉም ኮሚሽኑ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ግድያውን ለመመርመር የተዋቀረውን የምርመራ ቡድን እንዲሁም የከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል፡፡

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ ምርመራ መጀመሩን  ተገንዝቧል፡፡ በምርመራ በሂደቱም እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው አንደሚገኝ  ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን የማቆያ ቦታ በመጎብኘት አረጋግጧል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ የተሻለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ክፍተቶችንም መኖሩንም አልሸሸገም፡፡

በአካባቢው ማኅበረሰብ በግድያው ላይ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን የተጠቆሙ፣ አልያም በድርጊቱ ዋነኛ ፈጻሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ገና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ወይም ምርመራ እየተደረገባቸው አለመሆኑን ምክንያታዊ አሳማኝ ሁኔታዎችን መገንዘቡን ይፋ ያረገው ኮሚሽኑ  ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ጭምር ያሉ በመሆናቸው በምርመራ ሂደቱ ላይ ጫና እያደረሱ መሆናቸውን ወይም ለሂደቱ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው የፀጥታ እና የአስተዳዳር አካላትም ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቂ ትብብር እያደረጉ እንዳልሆነ ተዓማኒ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል ፡፡ በሌላ በኩል የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ፣በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆኑን  አረጋግጪያለው ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ 

የኮሚሽኑ መግለጫ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከከራዩ ማህበረሰብ ጋር የእርቅ ሂደት ለማካሄድ መዘጋጀቱን ማስታወቁን ተከትሎ ነው የወጣው።  የክልሉ መንግሥት የኮሙኒኬሺን ቢሮ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ እየተካሄደ ካለው የወንጀል ምርመራ ሥራ ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል የአባገዳዎች ምክር ቤት አስተባባሪነት በክልሉ መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ሽምግልና እየተካሄደ መሆኑን ተናግሯል፡፡ 

ኮሚሽኑ መንግሥት በሕዝቡ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ በእርቅ እንዲፈታ ጥረት ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የእርቅ ሂደቱ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ሊያስቀር ስለማይችል የሕግ ተጠያቂነት ሂደቱ ሊደናቀፍ እንደሌለበት ተናግሯል፡፡ የእርቅ ስርአቱ በተጎጂዎች፣ በተጎጂዎች ቤተሰቦችና በአካባቢው ማኅበረሰብ ሙሉ ፈቃድና ተሳትፎ ሊሆን ይገባልም ብሏል።የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የተጎዱትን መካስ፣ ዕርቅና ሰላም፣ ፍትሕና ተጠያቂነት በአንድነት ሊተገበሩ የሚችሉና የሚገቡ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለዚህ አይነት የተሟላ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.