ዜና: የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እርማት ላይ ስህተት መፈጠሩን እንዳረጋገጠ አስታወቀ

መጋቢት 14፣ 2014፣ አዲስ አበባ፣የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዛሬ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የ2013 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ይፋ አድርጓል። በመግለጫውም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በተለይም በሁለተኛው ዙር በተሰጠው ፈተና እርማት ላይ ስህተተ ስለመፈጠሩ ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ማረጋገጡን አስታውቋል።

በመግለጫው እንደተነገረው በፈተና ወቅት የተፈጠሩ የእርማት ስህተቶች በድጋሚ እንዲታይላቸው ቅሬታቸውን ለፈተናዎች ኤጀንሲ ቢያቀርቡም  ቅሬታቸውን  ተቀብሎ ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸው ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የፈተናዎች ኤጀንሲ ነው በሚል ቅሬታቸውን ሳይቀበል የቀረ መሆኑን እና በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ለእንግልት  መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ በመግለጫው በፌደራል የአስተዳደር ስነ ስርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 20፣21፣22፣23 እና ተከታዮቹ  መሰረት  ማንኛውም ዜጋ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ ለሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ተቋም የማቅረብ መብት እንዳለውና ቅሬታ የቀረበበት ትቋምም ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ጠቅሶ የፈተናዎች ኤጀንሲ እና ትምህርት ሚኒስቴር ግን በአዋጅ የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንዳልተወጡ እንዲሁም ከአዋጅ ቁጥር 1183/2012 አኳያ አስተዳደራዊ በደል መፈፀማቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በተጨማሪም የሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ ለቀረቡለት ከ20,000 በላይ የኦላይን (online) ቅሬታዎች የሰጠው ምላሽ የቀረቡትን  ቅሬታዎች በመለየት ሳይሆን ለሁሉም ቅሬታዎች ተመሳሳይ “ቅሬታው የታየ” መሆኑን መግለፁ ለአቤቱታ  አቅራቢዎች ቅሬታን እንደፈጠረ  በመግለጫው አስታውቋል። 

አያይዞም የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው  በሚሰጥበት ወቅት  የጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች በነበረባቸው አካባቢዎች ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች ”በልዩ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ሊወሰንልን ይገባል” በሚል የቀረበውን ጥቆማ በሚመለከት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ላይ በልዩ ሁኔታ ሊታይ የሚችል ጉዳይ እንደሌለ ማሳወቁን አስመልክቶ በምርመራዬ ደርሼበታልሁ ያለውን ሲገልፅ “ ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በተሰጠበት ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በአፋር፣አማራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች የነበሩ መሆኑ በመንግስት በይፋ የሚታወቅ ነው” በማለት አብራርቷል፡፡

ስለሆነም ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች ለሚቀርቡ አቤቱታዎችን ግልጽ እና ምክንያታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተቋሙ በመግለጫው አሳስቧል። 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ስህተት መፈጠሩን ገልፆ  አጣሪ ቡድን ወደ ፈተናወች ኤጀንሲ መላኩን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡  የክልሉ ትምህር ቢሮ መጋቢት 9 ቀን  በ2013ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ጊዜው እንዲራዘም ጠይቋል፡፡

የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን በሰሜን ወሎ ዞን ከሚገኙ 42 ትምህርት ቤቶች በስድስት ትምህርት ቤቶች ለትምህርት መልቀቂያ ፈተና ከተቀመጡት 679 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት መውደቃቸውን የገለፀ ሲሆን ይህም የውጤት አወሳሰዱን ከመደበኛ ስርዓት ውጭ መሆኑን ዘግቧል።እነዚህ ድርጊቶች የተስተዋሉባቸው ትምህርት ቤቶች ጊራና ካሊም ፣ቁል መሰቅ ፣ጉርጉር ደብረሮሃ ፣ሃናሙቃት ደብረሲና እና ከበበው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በተጨማሪም የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ፈተና እና አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ሙሉ አዳነ እንደገለፁት ዞኑ በጦርነት ውስጥ ከገባ ከ5 ወራት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን አሁንም በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ለፈተና ለመቀመጥ ሙሉ ዝግጁነት እንዳነበራቸው ተናግረዋል። ተማሪዎች በጦርነቱ ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጉዳት ሳያገግሙ ፈተና መውሰዳቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል። ዞኑ ለፈተና ከተቀመጡት 9ሺህ 710 ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡት 3ሺህ 567 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል።የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በርካታ ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱን ገልፆ በአሁን ሰዓትም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራሮቸና ባለሙያዎች፣ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና መምህራን የተውጣጣ ቡድን ወደ ፈተናወች ኤጀንሲ መላኩን አስታውቋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.