ዜና: በሰሜን ወሎ ዞን በጦርነቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸው የወደማባቸው ከ34ሺ ሰዎች በላይ በዳስና በኬንዳ እየኖሩ ነው ተባለ

አዲስ አበባ: ግንቦት 17/2014- በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ  በጦርነቱ ምክኒያት 6245 ቤቶች በመውደማቸው ከ34000 በላይ ሰዎች በዳስና በኬንዳ እየኖሩ ነው ሲል የወረዳው የከተማና መሰረተ ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ምሳው በዛ የህወሀት ሀይሎች ወረዳውን ከ5 ወር በላይ ይዘውት በነበረበት ወቅት በመንግስትና የህዝብ ሃብትና ንብረት ላይ የፈጸመው ዘረፋና ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ከህወሀት ሀይሎች ጋር በተደረገው ጦርነት 6245 ቤቶች በጦርነት በመውደማቸው 34736 ሰዎች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በዳስ ፣ በኪራይና በዘመድ ቤት ተጠግተው ለመኖር ተገደዋል ሲሉ ገልፀዋል።

ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ሰዎች መልሶ ለማቋቋም ከወረዳው አስተዳደር ምክርቤት አቅም በላይ በመሆኑ ለወረዳው የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መምጣቱን ገልፀው የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የዞንና ለክልል ሃላፊዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደረጉልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም ሲሉ ሃላፊው አክለዋል፡፡

የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ  የወረዳው የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ነበረ ህይወታቸው ለመመለስ መንግስትና ረጂ ድርጅቶች በመልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የጽ/ቤቱ ሃላፊ  አቶ ምሳው በዛ ጥሪ አስተላልፈዋል።አስ

 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.