ዜና፦ የኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ መፈናቀል እና ህገ-ወጥ እስራት የመብት ጥሰት መፈጸማቸውን አስታወቀ

በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ በርካታ ማረሚያ ቤቶች የሥነ ምግባር ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ ታራሚዎች አካላዊ ቅጣት የሚቀጡ መሆኑ በሪፖርቱ የተመዘገበው ሌላው የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ። ምስል፡ ኢሰመኮ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1፣ 2014 ዓ.ም ፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው የሀገሪቱ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ በታጠቁ ኃይሎች፣ በኢመደበኛ ቡድኖች እና በግለሰቦች በሲቪል ሰዎች ላይ ብሔርን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ፤ የግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል እና የንብረት ማውደምና ዘረፋ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አስታወቀ።

በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ዘገባ ኢሰመኮ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ወቅታዊ አውድ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በፍጥነት ተለዋዋጭ መሆኑን ገልፆ ዓመታዊ ሪፖርቱ በሚሸፍነው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ እና በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰታቸውን አብራርቷል፡፡

ኮሚሽኑ” እጅግ አስከፊ” የሆኑ በማለት ያመላከታቸውን የበርካታ ሰዎች ሞት፣ የአካልና ሥነልቦና ጉዳት፣ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ መፈናቀልና፣ ንብረት ውድመት ጥሰቶች በመንግሥት ኃይሎችና ከመንግሥት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎችና ቡድኖች በጦርነትና ግጭት አውድ ውስጥ የተፈጸሙ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችንም ጨምሮ በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሪፖርቱ በዝርዝር አብራርቷል፡

በኮሚሽኑ ከተጠቀሱት የመብት ጥሰቶች መካከል “በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት በሴቶችና ሕጻናት ላይ የደረሰውን ስልታዊና መጠነ ሰፊ የሆነ የፆታና ወሲባዊ ጥቃት በተመለከተ የአጥፊዎች ተጠያቂነት አለመረጋገጥ፣ የተጎጂዎች የመካስ መብት አለመጠበቅ፣ በቂ የጤና እና የሥነልቡና ድጋፍ አገልግሎት አለመኖር፣ የቅድመ ጥንቃቄ እና የአስቸኳይ ምላሽ ሥርዓት አለመዘርጋት፣ መልሶ የማቋቋም ሥራ በፍጥነትና በልዩ ትኩረት ለሁሉም እኩል ተደራሽ በሆነ መልክ አለመሰራት እና የዚህ አይነቱ ጥቃት ስጋት የቀጠለ መሆኑ ተስተውሏል” በማለት ዘግቧል።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ በሲቪል ሰዎች ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል ያለ ሲሆን ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሕይወት የመኖር መብት፣የአካል ደኅንነት መብት፣ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ከጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶች ጥሰቶች በመንግሥት ወታደሮች፣ በሕወሓት ኃይሎችና በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች እንደፈፀሙም አስታውቋል።

እንደሪፖቱ በነበረው ጦርነት ተጎጂዎች በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች ሲሆኑ፣ በጦርነት ተሳታፊ የነበሩና የተማረኩ ተዋጊዎችም ለመብት ጥሰቶች ተጋልጠዋልም ብሏል። በሌሎችም የሃገሪቱ ክልሎች በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎችና መደበኛ ባልሆኑ የእስር ቦታዎች ከጦርነቱ ጋር በተያየዘ በታሰሩ ሰዎች ላይ “ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር እና ድብደባ” ተፈጽሟልም ብሏል፡፡

በዚሁ አመታዊ ሪፖርትም ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘፈቀደ እስራት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰር፣ የቤተሰብ እና የሕግ አማካሪ ጉብኝትን መከልከል እንዲሁም ምርመራ ሳይጀመር የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት በሰፊው ተስተውሎ እንደነበርም ተካቷል።

በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የተካሄደው ጦርነት በአካባቢዎቹ በመሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ፣ በጤና እና በትምህርት ተቋማት ላይ ውድመት አስከትሎ እንደነበር የጠቀሰው የኢሰመኮ ሪፖርት ጦርነቱ የንብረት መውደምን፣ መፈናቀልን፣ የምርት መስተጓጎልን፣ እንዲሁም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን እንዳስከተለም ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ከልሎች የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በድርቅ በመጠቃታቸው ምክንያት በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ድጋፍ የመስጠት አቅም ላይ ጫና ያሳደረ መሆኑን ሪፖርቱ አካቷል፡፡ኢሰመኮ አያይዞም በአሁኑ ሰዓት ከ4 ሚልየን በላይ የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሳታፊ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሹ እና የእርዳታ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሷል።

በጦርነቱ ወቅት “በተለይም የአዕምሮ ሕሙማን (የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት ያለባቸው ሰዎች) ከሌሎች ሲቪል ሰዎች በበለጠ የጥቃት ዒላማ መደረጋቸው በዚህ ዘገባ ውስጥ ይገኛል

የአመለካከት፣ ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል መሰረት፣ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ወቅቶች፣ በትግራይ ክልል 15 የሚድያ ሠራተኞችን ጨምሮ 54 የሚዲያ ሠራተኞች ተይዘው ከቀናት እስከ በርካታ ወራት ለሚሆን ጊዜ በእስር መቆየታቸውን አመላክቷል፡፡

“በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ በርካታ ማረሚያ ቤቶች የሥነ ምግባር ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ ታራሚዎች አካላዊ ቅጣት የሚቀጡ መሆኑ እንዲሁም በቅጣት መልክ ወደ ማግለያ ክፍል የሚገቡ ተጠርጣሪዎች ሕክምና እና ሌሎች አገልግሎት ለማግኘት መድሎ የሚገጥማቸው መሆኑ። በተጨማሪም ታራሚዎች ወደ ማግለያ ክፍል እንዲገቡ የሚሰጠው ውሳኔ አሰጣጥ ግልጽነት የጎደለው፣ የይግባኝ ሥርዓት የሌለው እና ውሳኔው ተመልሶ የሚታይበት ጊዜ የማይቀመጥ በመሆኑ ተጠርጣሪዎች ለተራዘመ ጊዜ በማግለያው የሚቆዩበት ሁኔታ ያለ መሆኑ” በሪፖርቱ የተመዘገበው ሌላው የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው።

በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት “በተለይም የአዕምሮ ሕሙማን (የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት ያለባቸው ሰዎች) ከሌሎች ሲቪል ሰዎች በበለጠ የጥቃት ዒላማ መደረጋቸው። ጦርነቱ በተከሰተባቸው ክልሎችም ሆነ ተደጋጋሚ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና ድርቅ በተከሰተባቸው በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተደጋጋሚ የአቅርቦት መስተጓጎሎች የሚያጋጥሙት መሆኑ፣ ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አለመሆኑ እንዲሁም በማከፋፈል ሂደቱ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሠራር አለመኖሩ” በዚህ ዘገባ ውስጥ ይገኛል:: አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.