አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 ፣ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የሳምንታዊው “ፍትሕ” መጽሔት መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የህግ መንግስት እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሶስት ተደራራቢ የወንጀል ክሶች መሰረተ።
ክሶቹም “የአገር መከላከያ ሚስጥር በማውጣት”፣ “በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሀሰት ወይንም የሚያደናግር መረጃ በማውጣት”፣ “ወንጀል በማነሳሳትና በመገፋፋት” ናቸው።
በዚህም መሠረት ፣ 1ኛ ክስ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 44(1)፣ (2) እና 336(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ “የአገር መከላከያ ሚስጥር በማውጣት” ሲሆን ፣ 2ኛ ክስ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 44(1)፣ (2) እና 337(1) ስር የተመለከተውን “በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሀሰት ወይንም የሚያደናግር መረጃ በማውጣት” በመተላለፍ እና ፣ 3ኛ ክስ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 44(1)፣ (2) እና 257(ሠ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ፣ “ወንጀል በማነሳሳት እና በመገፋፋት” የሚል ሶስት ተደራራቢ ክስ አቅርቧል።
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን ለጋዜጠኛ ተመስገን የየ10 ሺህ ብር ዋስትና መብት ቢፈቀድለትም፣ መርማሪ ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዋስትና በተሰጠበት እለት ከስአት ይግባኝ አስገብቶ ነበር።
በዚህም መሠረት እሮብ ሰኔ 1 ቀን፣ መርማሪ ፖሊስ ምርመራወን ሳይጨርስ ዋስትና መሰጠቱ አግባብ አይደለም፣ “ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ከወጡ የምርመራውን ሂደት ያበላሹብኛል” በማለት እንዲሁም “በህዝብ ላይ የደረሰ ከፍተኛ ጉደት” እንዳለ ለፍርድ ቤት አስረድቶ የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝ ተሽሮ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።
ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሰጠውን ትእዛዝ በመሻር ለመርማሪ ፖሊስ ከግንቦት 30 ቀን ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን ተጨማሪ 8 ይምርመራ ቀናት ሰጥቶ ጉዳዩ በስር ፍርድ ቤት እንዲታይ ብሎ ብይን ሰጥቷል።
በሰኔ 7፤ 2014 ችሎት ላይ ዐቃቤ ህግ ተመስገንን “ወታደራዊ ምስጢሮችን ለማይመለከተው አካል በግልጽ በመጻፍ” ወንጀል እንደጠረጠረው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ከዚህ በተጨማሪም “የተቋሙን እና የሰራዊቱን መልካም ስምና ተግባር በማጥፋት” ፣ እንዲሁም “የሰራዊቱን ሞራል ለበማሳነስ በተቀናጀ ዘዴ” በመንቀሳቀስ መጠርጠሩን ገልጾ ነበር።
በዛሬው ችሎት ላይ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ በደንበኛው ላይ የቀረቡበት ክሶች ሰፋ ያሉ ስለሆኑ የክስ መቃወሚያዉን “ከደንበኛዬ ግር ተነጋግሬ” በፅሁፍ እዳቀርብ ይፈቀድልኝ ሲል ፣ በተጨማሪም ክሶቹ ዋስትናን የማያስከለክሉ ስለሆነ ዋስትና እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል።
ከዚህም በላይ ደንበኛቸው ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ስርአት ለሶስት አመታት በዋስትና ወቶ ክሱን ሲከታተል እንደቆየና ይህም የደንበኛውን ህግ አክባሪት ያሳያል ሲል ለችሎት አስረድቷል።
ቢሆንም አቃቤ ህግ ዋስትናውን የተቃወመ ሲሆን “ጋዜጠኛው ላይ ተደራራቢ ክስ ነው የመስረትነው”፣ 1ኛው ክስ እስከ 10 አመት ያስቀጣል 2ተኛው ከ12 አመት እስከ እድሜ ልክ ያስቀጣል፣ 3ተኛው ክስ 10 አመት የሚያስቀጣ ስለሆነ ተከሳሹ በዋስትና ቢወጣ ተመልሶ ሊቀርብ ስለማይችል ዋስትና መሰጠቱን እቃወማለው በማለት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት ለአርብ ሰኔ 24 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። አስ