አዲስ አበባ፡- በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ እና ሌሎች ሶስት ሰራተኞች ከሁለት ፋብሪካዎች 29 ሺህ 2 መቶ ኩንታል ሲሚንቶ በተቋሙ ስም በዝቅተኛ ዋጋ ገዝተው በውድ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሲል የሙስና ክስ መመስረቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኃላፊዎቹ እና ኤክስፐርቶቹ ግዥውን የፈጸሙት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስም ሲሆን በ2013 እና 2014 ዓ.ም በመስሪያ ቤቱ ስም ካወጡት የስሚንቶ ሺያጭ ለግል ጥቅማቸው ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ፍትህ ሚኒሰቴር ባወጣው መግለጫ ተመልክቷል።
ተከሳሾቹ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ፣ የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ግዥ መምሪያ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ እንደዚሁም አቶ ቱጁባ ቀልበሳና አቶ ሙስጠፋ ሙሳ የተባሉ የግዥ ሰራተኞች መሆናቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው እንዳመለከተው 1ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ደሜ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋሙ ሲሚንቶ የመግዛት ፍላጎት እንዳለው በማስመሰል በድምሩ 29 ሺህ 2 መቶ ኩንታል ሲሚንቶ ከደርባንና ከዳንጎቴ ፋብሪካዎች እንዲገዛ በማድረግ 7 ሺህ 2 መቶ ኩንታል በ3ኛ ተከሳሽ አቶ ቱጁባ ቀልቤሳ እና 22 ሺህ ኩንታል ደግሞ በ4ኛ ተከሳሽ አቶ ሙስጠፋ በህገወጥ መንገድ እንዲሸጥ አድርገዋል ብሏል።
መግለጫው አክሎም ሲምንቶወ ከፋብሪካዎች እንዲገዛ የተደረገው በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም ለአስቸኳይ የግንባታ ስራዎች ሲምንቶ እንደሚፈልግ ተደርጎ በ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ስም ደብዳቤ ተጽፎ በእነዚሁ ተከሳሾች የግል ሒሳባቸው ክፍያ በመፈፀም እንደሆነ ያትታል።
2ኛ ተከሳሽም አቶ አሸናፊ ተስፋዬ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ የፃፉትን ደብዳቤ ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲያደርሱ እና በተቋሙ ስም የተገዛውን 29 ሺህ 2 መቶ ኩንታል ሲሚንቶ እንዲሸጡ እንዳዘዙ መግለጫው ጠቁሟል።
እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፣ ተከሳሾቹ ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስም ከላይ የተጠቀሰውን ብዛት በመግዛት በጥቁር ገበያ በ30 ሚሊዮን 99 ሺህ 3 መቶ 60 ብር በመሸጥና ለግል ጥቅማቸው በማዋል በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በመግለጫው መሰረት ተከሳሾቹ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ፊት ቀርበው ክሱ እንደተነበበላቸው እና በተመሰረተባቸው ክስ መቃወሚያቸውን ለታህሳስ 7 ቀን 2015 ዓም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በህዳር ወር አጋማሽ ላይ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት የጀመረውን የፀረ ሙስና ዘመቻ የማስተባበር፣ ቀደም ሲል በጥናት ከተለዩት በተጨማሪ ተዋናዮችን የመለየት እና ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገው ነበር።
አዲስ የተቋቋመው ሀገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ በህዳር ወር ቀን 2015 ዓ.ም. ስራ መጀመሩን ገልጾ በሙስና እና በተደራጀ ሌብነት ላይ ከፍተኛ እርምጃ መወሰድ እንደጀመረ አስታውቆ ነበር።
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራው ብሄራዊ የሙስና ኮሚቴ በሙስና የሚጠረጠሩ ከመሬት አስተዳደርና ከመንግሥት ቤቶች አስተዳደር፣ ከጸጥታና ፍትህ ተቋማት፣ ከፋይናንስ ዘርፍ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖራቸውን ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር በመሆን የኮሚቴውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። አስ