ዜና፡ በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት ተቋሙ የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አጋጥሞኛል አለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/ 2015 ዓ.ም፡­­- በ2014 ዓ.ም ብቻ ከኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ 756 ቶን ብረት መዘረፉን እና በዚህም የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የምስራቅ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው በ2014 ዓ.ም ብቻ 24 የሚደርሱ ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊ የብረት ማማዎች ሙሉ ለሙሉ ተቆርጠው የወደቁ መሆኑን ጠቅሰው የብረትና የኮንዳክተር ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው እና በቁጥር 30 ሺ 257 የሚሆኑ የተለያዩ የታወር ብረቶች ደግሞ በቁማቸው ካሉ ማማዎች ተፈታተው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከወደቁትና በቁማቸው ከተዘረፉት ማማዎች 756 ቶን ብረት መሰረቁን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይህም በገንዘብ ሲሰላ 72 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ መድረሱንና የተሰረቀውን ብረት መልሶ ለመተካት ተቋሙ 23 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ማወጣቱን አስታውቀዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም በስርቆት፣ በመልሶ ግንባታና ከአገልግሎት መቋረጥ ጋር ተያይዞ የባከነውን 2 ሺ 396 ሜጋ ዋት ሰዓት ኃይል ጨምሮ ተቋሙ ከመቶ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ኪሳራ እንዳጋጠመው ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው ስርቆትን ለመከላከል ከህብረተሰብ ተወካዮች፣ ከጸጥታ እና ከፍትህ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ውጤት እያስገኘ መምጣቱን ተናግረው በአንዳንድ አካባቢዎች በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ትብብር ወንጀሉን ለመከላከል ቢሞከርም በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ችግሩ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተከሰው በሚቀርቡ ወንጀለኞች ላይ የፍትህ አካላት የሚጥሉት ቅጣት አስተማሪ አለመሆኑና ግብዓት ለማግኘት ሲሉ ስርቆቱን የሚደግፉና የሚረከቡ የብረታብረት ፋብሪካዎችና ባለሀብቶች እንቅስቃሴ ሊፈተሸ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.