ዜና፡ የፌደራል ፖሊስ በመስከረም አበራ ላይ ክስ ለመመስረት 14 ተጨማሪ ቀን ጠየቀ

በብሩክ አለሙ @birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/ 2015 ዓ.ም፡- የፌደራል ፖሊስ መስከረም አበራ በማህበራዊ ገፅ እና ኢትዩ ንቃት በተሰኘ የራሷ ሚዲያ ህግ መንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና በመከላከያ ሰራዊት ላይ እምነት እናዳይኖር ለማድረግ እንዲሁም በአዲስ አበባ የመዝሙርና ባንዲራ ጉዳይ ላይ እና በጉራጌ ዞን በተነሳው ግጭት ላይ ቅስቀሳ በማድረግ ወንጀል መጠርጠሯን ለፍርድ ቤት ማስረዳቱን ጠበቃዋ አቶ ሰለሞን ገዛሀኝ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው ዪትዩብ ቻናል መስራች እና ባለቤት የሆነችዉና በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሃሳብ በመስጠት የምትታወቀዉ መስከረም አበራ ትላንት ታህሳስ 6 ቀን 2015 ዓ.ም.  የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረበች ሲሆን በችሎቱም የፌድራል ፖሊስ ክስ ለመመስረት ይረዳው ዘንድ ወደ ጉራጌ ዞን በማምራት የሰው ምስክር ለማሰባሰብ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን ጠይቋል ሲሉ ጠበቃው አክለው ገልፀዋል፡፡

የመስከረም ጠበቃ ፖሊስ የተጠርጣሪዋ ቤት በመግባት የሰነድ ማስረጃዎችን በመውሰዱ 14 ተጨማሪ ቀን አያስፈልግም በማለት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን ፈቅዶ ለታህሳስ 20/ 2015 ዓ.ም ምንም ምክንያት ሳያቀርብ የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ እንዲቀርብ ዝዕዛዝ አስተሏልፏል፡፡

መስከረም አበራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ከሶስት ቀናት በፊት ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም  ከሰዓት 10፡30 አካባቢ ሃያ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከባለቤቷ ጋር ሳሉ ሲቪል እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች ነው፡፡

መስከረም የግለሰቦቹን ማንነት ስትጠይቅ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት ይዘዋት እንደሚሄዱ ተናግረው በመኪና እንደወሰዷት ባለቤቷ ፍጹም ገ/ሚካኤል ለቢቢሲ አስረድቷል።

መስከረም አበራ ግንቦት 12/ 2014 ዓ.ም በፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውላ የነበር ሲሆን፣ ፖሊስ “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እና የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልልን ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት እንደምትሰራ” ጠርጥሬያታለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡

በኋላም ፍርድ ቤቱ የቀረበባት ክስ የዋስ መብት የማያስከለክል በመሆኑ በ 30 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንድትፈታ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡  መስከረም ሰኔ 6 /2015 ዓ.ም ከተፈታች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ  ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ዳግም ታስራለች፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.