ዜና፡ የ12 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛቸውን ገድለው በድብቅ ሊቀብሩ ሲሉ የተያዙት ባል እና ሚስት በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/ 2015 ዓ.ም ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ባለትዳሮች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታህሳስ 17/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 17/2014 ዓ.ም ባለ ጊዜ ውስጥ የ12 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛቸው ላይ ጥቃት በመፈፀም ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረጋቸው በ25 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ልጃለም ጌታቸው ታዬ እና ቆንጂት ሙለታ በቀለ የተባሉት ባልና ሚስት ተከሳሾች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታህሳስ 17 እስከ ጥር 17/2014 ዓ.ም ባለ ጊዜ ሟች አስቴር ነገሰን በተደጋጋሚና በተለያየ ጊዜ በፍልጥ እንጨት፣ በእርግጫ፤ በሞባልይ ቻርጀር ገመድ ጀርባዋን፣ ወገቧን እና እግሯን ደጋግመው በመደብደብ፤ ከገደሏት በኋላ የሟችን አስከሬን በሳጥን በማድረግ በድብቅ ለመቅበር ሲሰናዱ ተይዘዋል፡፡

ምርመራ ሲጣራ በሟች ላይ በርካታ የቆዳ መጋጋጥ እና የመበለዝ፣ ከአንገትዋ የፊተኛው ክፍል አንስቶ ወደ ቀኝ እና ግራ ትከሻዋ የተሰራጨ የመበለዝ፣ በደረትዋ የላይኛው ፊተኛና ጎን 1/3 ክፍል የመበለዝ፣ በቀኝና በግራ ቂጥዋ ጭን የላይኛው ኋለኛ ክፍል እና በጀርባዋ የታችኛው ክፍል ላይ በርካታ የቆየ የቆዳ መጋጥ፣ በራስ ቅልዋ ፊተኛ መካከለኛ ክፍል የመበለዝ፣ በእጅ እና እግሮቿ ላይ ወደ ውስጥ ደም የመፍሰስ፣ የመሰራጨትና የመበለዝ ጉዳት ምክንያት ህይወቷ ማለፉ በማስረጃ በመረጋገጡ ዐቃቤ ህግ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ተከሳሾችም በችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸው ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ብለው የተከራከሩ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አስደግፎ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያረጋገጠ በመሆኑ እና ተከሳሾችም ይህን የዐቃቤ ህግ ክስ እና የቀረበባቸውን ማስረጃ አንዲያሰተባብሉ በተሰጠ ብይን መሰረት 2 የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ሰጥቶ ቅጣት ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ሁለቱም ተከሳሾች ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው በእርከን 37 ስር እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ እና እንዲሁም ተከሳሾች ለ5 ዓመት ከመብቶቻቸው እንዲሻሩ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.