ሃምሌ 1፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦የከተማ አስተዳደሩ ግንባታቸው ሲካሄዱ የቆዩ 14ኛው ዙር የ20/80 እና 3ኛው ዙር የ40/60 በአጠቃላይ 25,491 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመዝጋቢዎች፣ እና የክብር እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ በይፋዊ የዕጣ ስነ ስርዓት አስተላልፏል፡፡
በዚህ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የ20/80 ባለ 3 መኝታ ቤቶች አለመካተታቸው በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ወሃቢረቢ የገለፁ ሲሆን የባለሶስት መኝታ ቤት በተመለከተም ባለፈው ዙር ዋጋውን እስከ 1500 ብር ቁጠባ ድረስ በማውረድ በማስተናገድ የቤቶች ቦርድ ፕሮግራሙን መዝጋቱን አስታውሰው ፤በዚህ ዙር ለማስተናገድ አጠቃላይ ሲስተሙን የሚያዛባ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑ ተገፀዋል፡፡
ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶች፣ የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም አያት 2፤ ቦሌ በሻሌ፤ ቡልቡላ ሎት 2 ሲሆኑ በ20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም ደግሞ በረከት፤ ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፤5፤6)፤ ወታደር፤ የካ ጣፎ፤ ጀሞ ጋራ፤ ጎሮ ስላሴ፤ ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል መሆናቸው ተገልጧል፡፡
ከንቲባ አዳነች 14 ኛዉን የ20/80 እንዲሁም 3ኛ ዙር የ40/60 የመኖሪያ ቤት እጣ የማዉጣት ፕሮግራም ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር፤ የአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የቤት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ አገላለፅ ከ2011 ጀምሮ በግንባታ ላይ የነበሩ ከ139ሺ በላይ ቤቶች ሲሆኑ ከ21.57 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መሰረታዊ ስራዎች በማጠናቀቅ 96.918 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ቁልፍ ለማስረከብ ፣ ከዚህ ውስጥ ለ54ሺ በላይ ባለዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ መደረጉን ገልፀው የቀሩትም መጥተው ቁልፋቸውን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም ያለዉን ሰፊ የቤት ፍላጎት ለማሟላት አዲስ እይታ መኖሩን የገለጹት ከንቲባ አዳነች የመኖሪያ ኅብረት ስራ፣ በመንግስትና በባለሀብቶች ትብብር፣ በሽርክና ፣በሪል ኢስቴት ፣ እንዱሁም በግለሰብ ደረጃ በሚከናወን የቤት ባለቤትነት የከተማዋን የቤት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮቾችን በመጠቀም በቴክኖሎጅ የተደገፈ የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ መርሀ ግብር መኖሩን ጠቁመዉ እስካሁን 10 ሺ ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡ ይህም የአስተዳደሩን በቤቶች ዘርፍ ያለዉን ችግር ለመቅረፍ ያለዉን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዛሬው እለት እጣ የሚያወጣባቸውን ቤቶች የሚያስተዳድረው ቴክኖሎጂ ሲስተም እንደከዚህ ቀደሙ ለተለያየ ህገወጥ ድርጊት እንዳይጋለጥ ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ የተሰራ መተግበርያ በመሆኑ ይህም አስተማማኝና ግልፅነት እንዲሁም ፍትሃዊ አሰራር የዘረጋ ነው ተብሏል፡፡ የቅድሚያ ተጠቃሚነት አወሳሰን በፍትሃዊነት የሚተገብር ሲሆን ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት በእጣው ላይ በፍትሃዊነት አካቶ ሊያወጣ በሚችል መንገድ የተሰራ ነው፡፡
በተጨማሪም ቴክኖሎጂው፤ አጠቃላይ የቤት ፈላጊዎችን መረጃና ለዕጣ የተዘጋጁ ቤቶችን መረጃ ይይዛል፣ ዕጣ ሲወጣ በቀጥታ የአሸናፊዎችን ሙሉ መረጃ እና የቤት መረጃ እንደሚያሳይ፣ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ የአሸናፊዎችና የቤታቸውን መረጃ ያለ ሰው ንክኪ በቀጥታ እንደሚያሳይና ለህትመትም እንደሚያዘጋጅ ሲሆን የተዘረጋው ሲስተም ማንም እንደፈለገ ገብቶ ማስተካከል ሌላ ሰው መጨመርም መቀነስም Edit ማድረግ የሚከልክል ሲሆን በተቃራኒው ሂደቱን በመቆጣጠር Audit ደግሞ ስርዓቱን ራሱ ከህገወጥ ድርጊቶች የሚጠብቅ ሲሆን አንዴ እጣው ከወጣ በኋላ ለሌላ ንክኪ እንዳይጋለጥ ራሱን ዝግ የሚያደርግ ሲስተም መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡አስ