ዜና፡ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ለማደስ የሰላም ስምምነቱ በዘላቂነት መተግበር ላይ የተመረኮዘ መሆኑን አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም፡- የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ትላንት ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ለማደስ እና ሀገሪቱን ለማገዝ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። ህብረቱ በመግለጫው እንዳመላከተው ግንኙነቱን ሙሉ ለሙሉ ለማደስ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፤ ቅድመ ሁኔታውም የፌደራል መንግስቱ ከትግራይ ሀይሎች ጋር የደረሱት ስምምነት በዘላቂነት ተተግብሮ ካየሁት ብቻ ነው ብሏል።

ሁለቱም ሀይሎች ለስምምነቱ ትግበራ ያሳዩትን ቁርጠኝነት ያደነቀው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በተለይም የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ማድረጋቸው፣ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት መሻሻሉ እና ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን መቋቋሙን አወድሷል።

የህብረቱ ምክር ቤት በተጨማሪም የሽግግር ፍትህ ሰነድ መዘጋጀቱን በመልካምነቱ ገልጾ መንግስት ሰነዱ ከአለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ  ህጎች ጋር እንዲያቆራኛቸው ተነሳሽነት እንዲዎስድ ጠይቋል። ነገር ግን ምክር ቤቱ በድጋሚ ሁለቱም አካላት በፈጸሟቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የጦር ወንጀሎች እና አለም አቀፍ የሆኑ ህግጋት ጥሰቶች ላይ ገለልተኝነት፣ ግልጽነት፣ ያለው ምርመራ ማካሄድ ግዜ የማይሰጠው መሆኑን አስታውቋል።

በኦሮምያ እና በአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ውጥረቶች፣ ግጭቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ እንደሚያሳስቡት ያስታወቀው ምክር ቤቱ ውጥረቱን በማርገብ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጠይቋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.