ዜና፡ ምክር ቤቱ መከላከያ ሚኒስቴር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የውትድርና ስልጠና ወስደው ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያችል አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18 2015 ዓ.ም፡- መከላከያ ሚኒስቴር ዕድሜያቸው አስራ ስምንት ዓመት የሞላቸው እና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን በፈቃዳቸው ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ለሁለት ዓመት ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ሊያደርግ የሚያስችል አዋጅ ምክር ቤቱ አፀደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው ስብሰባ የተሻሻለውን የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ አጽድቋል፡፡  በዚሁ መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ ተማሪዎች በፈቃዳቸው በመደበኛ የመከላከያ ሠራዊት ወይም የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል አባላት የሚሆኑ ከሆነ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተያያዥ መብቶችንና ጥቅሞች እንዲጠበቁላቸው ያደርጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

መንግሥት አዘጋጅቶ ያቀረበው የተሻሻለ የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ የተጣለበትን ሀገር የመጠበቅ ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችል እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የተሻለ ሠራዊት ለመገንባት ማነቆ የሆኑ ሕግ ማዕቀፎችን እና ተቋማዊ አስተሳሰቦችን በመፈተሽ ለሀገር እና ሕዝብ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጧል፡፡

በተጨማሪም ይህ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ፣ ኅብረ ብሄራዊ ተዋጽዖውን የጠበቀ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ሠራዊት ለመገንባት ማነቆ ኾነዋል የተባሉ የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ያስችላል የተባለ ሲሆን፤ የሠራዊቱ አባላት የጡረታ መውጫ የእድሜ ጣሪያን አወሳሰን፣ የአገር ሕልውና ከባድ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ከሠራዊቱ የተገለሉ የቀድሞ አባላትን መልሶ መቅጠር የሚቻልበትና ሌሎች የሠራዊቱ መብትና ጥቅማ ጥቅሞችን አካቷል ነው የተባለው፡፡

ትላንት በዋለው ስብሰባም ምክር ቤቱ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1286/2015 አድርጎ በስድስት ድምጸ-ተኣቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.