አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣2014 ዓ.ም ፦ በደቡብ ጎንደር ዞን ከተጀመረው “የህግ ማስከበር ስራ” ጋር ተያይዞ ከ775 በላይ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ መግለፃቸውን የደቡብ ጎንደር ኮሚንኬሽን ቢሮ ዘገበ፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በርካታ የዞኑን ገፅታ የሚያበላሹና ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የሚያደርጉ “ፀረ ሰላም ሃይሎች” እየተበራከቱ በመምጣታቸው “ህግ የማስከበር” ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በተጀመረው የህግ ማስከበር ስራም 775 የወንጀል ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለህግ እንደቀረቡና የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
የትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ዞኑን ለቀው በወጡበት ማግስት የወንጀለኞች መበራከት፣ የግድያ፣ ተደራጅቶ መዝረፍ ፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና የመሳሰሉት ህገ ወጥ ድርጊቶች አስከፊ እየሆኑ በመምጣታቸው ህበረተሰቡ እጅግ በማማረር ህግ እንዲከበርለት በርካታ ጥያቄዎች ሲያነሳ የቆየ መሆኑን የገለፁ ሲሆን እየተከናወነ ባለው ህግ የማስከበር ስራም በርካታ ወንጀለኞች በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ብለዋል።
አክለውም በዞኑ የህግ ማስከበር ስራው ከተጀመረ ወዲህ የሰው ሞት፣የጥይት ተኩስና ሌሎች ወንጀሎችም በእጅጉ መሻሻላቸውንና ህዝቡ የእፎይታ ጊዜ ማግኘቱንም የጠቀሱ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ በማንኛውም ከተማ ከፀጥታ ሃይሉ ውጭ የታጠቁ ሃይሎች ባለመኖራቸው በከተሞች ላይ ሲታዩ የነበሩ መቀዛቀዞች ቀንሰው ሰው በነፃነት ተንቀሳቅሶ ስራውን እያከናወነ ነው ብለዋል።
አስተዳዳሪው አያይዘውም ከግንቦት 29 ቀን ጀምሮ በደስታም ሆነ በመከራ መሳሪያ ሲተኮስ የተያዘ ሰው ሙሉ ትጥቁ ለመንግስት ገቢ የሚሆን መሆኑን ገልፀዋል። በዞኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ህበረተሰቡ እየተማረረ መሆኑን ገልፀው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ቁጥጥር እንዲያደርጉና ያለ ታሪፋ የሚያስከፍሉ ህገ ወጦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይል ከ4,000 በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በመግለጫው በክልሉ በተጀመረው የህግ የማስከበር ተግባር 4,552 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንስተው እንደነበር ይታወሳል። ኃላፊው አክለውም እንደገለፁት የክልሉ የጸጥታ ሃይል አባላትን ጨምሮ ከ1,780 በላይ የሚሆኑት ተጠርጣሪዎች ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ናቸው፡፡ በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጭ በመሆን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው ክልሉን የበለጠ በማተራመስ የተጠረጠሩ አካላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።አስ