ዜና ትንታኔ፡ በእስር ላይ ከሚገኙት አምስት ጋዜጠኞች ለሶስቱ ዋስ ተፈቀደ፣ በሁለቱ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ቀን ተሰጠ

በማህሌት ፋሲል

አዲስ አበባ፣ግንቦት 30/2014 የፌደራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ  የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ትላንት በዋለው ችሎት የአምስት ጋዜጠኞችን ክርክር የሰማ ሲሆን የምርምራ መዝገቡን ለመመልከት ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቶ ነበር። አዲስ ስታንዳርድ  የክሱን ሂደት የተከታተለች ሲሆን እንደሚከተለው ተይባዋለች፡-

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፦ፍትህ መፅሄት

ትላንት በዋለው ችሎት የፍትህ መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ባለቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው 10 የምርምራ ቀን ለተለያዩ ባንኮች የተጠርጣሪውን የገንዘብ እንቅስቅሴ ለማወቅ “ደብዳቤ ልኬያለው ፣ መፅሄት ከሚታተምበት ማተሚያ ቤት የታተሙ መፅሄቶችን ወስደን ምርመራ እያደረግን ነው እንዲሁም ብጥብጥ ያስነሳል ያልነውን ፅሁፎች  ለምርመራ ወደ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት ልኬያለሁ” ያለ ሲሆን የምስክሮችን ቃል ለመቀበል እና የላካቸውን ደብዳቤ መልስ ተቀብሎ ምርመራውን ለመማጠናቀቅ 14 ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኛችን በእስር ላይ በቆየበት ጊዜ በተደጋጋሚ ሰብአዊ የመብት ጥሰት ሲደርስበት እንደነበር ለችሎት አስረድተው ከዚህ ቀደም ለፍርድ ቤቱ ደንበኛቸው የታሰረበት ለጤና ጠንቅ እንደሆነ አቤቱታ አቅርበው  ፍርድ ቤቱ  ፖሊስ እንዲያስተካከል ትእዛዝ ቢሰጥም እስካሁን ለውጥ እንደሌለ ይባስ ብሎ ደንበኛቸው ሀሙስ ግንቦት 25 ቀን  ድብደባ እንደደረሰበት ተናግረዋል። ጠበቆቹ አክለውም መርማሪ ፖሊስ ደንበኛቸው ከተጠረጠረበት ወንጀል አውድ ውጪ ያልሰራውን ወንጀል ካመነ ከእስር እንደሚወጣ ጫና እየተፈጠረበት ነው ያሉ ሲሆን ፖሊስ ከዚህ ቀደም ያላቀረበውን የምርመራ ጭብጥ አሁን እያቀረበ በመሆኑ  ደንበኛቸውን በእስር አቆይቶ ምርመራ ለማድረግ በቂ ምክንያት ስላልሆነ የደንበኛቸው የዋስትና መብቱ ተከብሮ ከውጭ ሆኖ ይከራከር  ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ  ተጠርጣሪው ላይ ምንም አይነት ድብደባ እንዳልደረሰ ገልፀው የማረሚያ ቤቱ እስር ቤቶች እድሳት ላይ ስለሆነ የክፍል ቅያሬ ለጋዜጠኛው ያልተደረገለት በዚህ መነሾ እንደሆነ  ለችሎት ተናግረዋል ። የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎት ለዛሬ የምርመራ መዝገቡ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር ተጠርጣሪው እና ጠበቆች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ቀርበው እንዲያስረዱ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። በዚህ መሰረት ዛሬ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ በችሎት ቀርቧል።

የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ10 ሺ ብር የዋስትና መብቱ ተከብሮ  ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ትእዛዝ ሰቷል። 

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ፦ሮሀ ሚዲያ

 የሮሀ ሚዲያ መስራችና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መአዛ መሃመድ ትላንት በችሎት  ከጠበቆቿ ጋር የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበች ሲሆን ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው 7 የምርመራ ቀናት የሰራውን ስራ እና ቀሪ ስራዎችን ለፍርድ ቤት አስረድቷል ።

መርማሪ ፖሊስ ከተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የተገኙ ፅሁፎችን ለብሄራዊ መረጃና  ደህንነት አገልግሎት  ቢሮ ምርመራ እንዲደረግ ልኬያለው ያለ ሲሆን የገንዘብ እንቅስቃሴውን ለማወቅ ለተለያዩ ባንኮች ደብዳቤ ልኮ በመጠባበቅ ላይ  እንደሆነና  ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሱ ንግግሮችን ከበይነ መረብ በማውረድ ምርመራ እያደረገ በመሆኑ የላካቸውን  የደብዳቤዎች  መልስ እና ቀሪ ስራዎችን ለመስራት 14 ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪዋ ጠበቃ በበኩሉ ፖሊስ ሁሉንም ምርመራ በማጠናቀቁ የደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድ ችሎቱን ጠይቀው ፖሊስ ምርመራውን ስላጠናቀቀ ተጨማሪ 14 ቀን መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ አንስተው ተከራክረዋል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ለዛሬ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ስጥቶ ነበር። ዛሬ መርማሪ ፖሊስ  የምርመራ መዝገቡን ለችሎት ያቀረበ ሲሆን የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ፍርድ ቤት ጋዜጠኛዋ በ10ሺ ብር ዋስ እንድትወጣ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ፦ገበያኑ

ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ  የ“ገበያኑ” የተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል መስራችና ባለቤት ሲሆን  ትላንት  የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ከመርማሪ ፖሊስ ጋር ክርክር አድርጓል ።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው 7 የምርመራ ቀን ለተለያዩ ባንኮች የተጠርጣሪውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለማወቅ ደብዳቤ እንደላከና ተጠርጣሪው ያደረጋቸውን ንግግሮች ከበይነ መረብ አውርዶ ምርመራ እያደረግ እንደሆነ ለችሎት አስረድቷል ። በቀጣይ ግብረ አበሮቹን ለመያዝ የ14 ቀን የምርመራ ቀን እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪው ጠበቃ በበኩላቸው የደንበኛቸውን ግብረ-አበሮች ለማያዝ በሚል ምክንያት ፖሊስ  በእስር ማቆየቱ አግባብ እንዳልሆነ አንስተው ደንበኛቸው  ሊጠየቅ የሚገባው በራሱ ስራ ብቻ እንደሆነ ለችሎት ተናግረዋል። አያይዘውም  ችሎቱ የደንበኛቸውን  የዋስትና መብት እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ለዛሬ እንዲቀርብለት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። በዚህም መሰረት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ ዛሬ  ቀርቧል።  የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ በ10 ሺ ብር ዋስ እንዲወጣ ትእዛዝ ሰቷል። 

ጋዜጠኛ መስከረም አበራ:- ኢትዩ ንቃት

“ኢትዩ ንቃት” የተሰኘው ዪትዩብ ቻናል መስራች እና ባለቤት ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ መስከረም አበራ ትላንት በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርባ ከመርማሪ ፖሊስ ጋር ክርክር አድርጋለች። 

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ብርበራ ማዱረጉንና ከመኖሪያ ቤቷ የውጭ አገር ገንዘብ ማግኘቱን እንዲሁም “ሁከትና ብጥብጥ” የሚያስነሱ ፅሁፎቹን እንዳገኘ ለችሎት አስረድቷል።ተጠርጣሪዋ የሚዲያ ባለቤት እንደሆነችና የሚዲያው ህጋዊነትን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ደብዳቤ መፃፋንና ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ እንዲሁም ለተለያዩ ባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴዋን ለማወቅ ደብዳቤ እንደላከ ለችሎት ግልጿል።  ከተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የተገኙ የሰነድና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል። 

የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኛቸው  በምርመራ ወቅት ይቀርስባት የነበረው ጥያቄ ስትፅፍ በነበርው ፁሁፎች  “የተለያዩ ከፍተኛ የጦር ጀነራሎችን አሸማቀሻል” የሚል እንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በደንበኛቸው ፅሁፍ “ተሸማቀኩ” የሚል አካል በሌለበት ሁኔታ ለፖሊስ  ተጨማሪ የምርመራ ቀን መስጠት የለበትም ያሉ ሲሆን  ደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድላት ችሎቱን ጠይቀዋል።

የሁለቱንም ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን እንዲያቀርብ ለዛሬ ትእዛዝ ሰጥቷል። ዛሬ የምርመራ መዝገቡን ይዞ ፖሊስ በችሎት የቀረበ ሲሆን የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ችሎት ለፖሊስ 6ተጨማሪ የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለሰኔ 6 ቀን  ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ፦ኢትዩ ፎረም 

“ኢትዩ ፎረም” የተሰኘው የዩትዩብ መገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ  በተመሳሳይ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ትላንት የቀረበ ሲሆን መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የ14ቀን የምርመራ ቀን ጠይቆበታል። 

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ10 የምርመራ ቀን የተለየያዩ ስራዎችን እንደሰራ ተናግሮ  ለባንኮችና ለተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስለተጠርጣሪው ማስረጃ ለማሰባሰብ ደብዳቤ እንደፃፈ እና በቀጣይ ለተጠርጣሪው የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ግብረ-አብሮቹን ለመያዝ እና ገንዘቡ ለምን አላማ እንደዋለ ለማጣራት ተጨማሪ የ14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል

የተጠርጣሪው ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው መከሰስ  ያለበት በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ መሆን እንዳለበት አንስተው የተከራከሩ ሲሆን ደንበኛቸው ለችሎት መናገር የሚፈልገው ጉዳይ እንዳለ አስረግጠው  ችሎቱ እንዲፈቅድለት ጠይቀዋል። ችሎቱም የጠበቆቹን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን ጋዜጠኛ ያየሰውም ለችሎት በምርመራ ወቅት ስለተጠየቀው  ሲናገር “በ2013 ዓ.ም የሞተን ሰው  በ2014 ዓ.ም በስልክ አናግረሀል”  ተብያለሁ  ያለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በአዋሽ አርባ በታሰረበት  ወቅት የሚቀርቡለት  ጥያቄዎች  አሁንም እንደሚቀርቡለት አስረድቷል።

 የተጠርጣሪው ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል። የሁለቱንም ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ለዛሬ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል ።

በዚህም መሰረት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ለችሎት ያቀረበ ሲሆን የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ፍርድ ቤት ለፖሊስ 6 ተጨማሪ የምርምራ ቀን ፈቅዶ ለስኔ 6 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ግንቦት 28 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ በማህበረሰብ አንቂዎች እና መሰል የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እየተወሰደ ያለውን እስር ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.