ዜና፡ በእስር ላይ ከነበሩት ጋዜጠኞች እስከ አሁን አራቱ በዋስ ተፈትተዋል

አዲስ አበባ፣ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ ከነበሩት ጋዜጠኞች እስካሁን አራቱ ከእስር በዋስ እንደ ተለቀቁ አዲስ ስታንዳርድ ማረጋገጥ ችላለች ። ከአራቱ ጋዜጠኞች መካከል ሁለቱ ዛሬ ተፈተዋል።

በዛሬው እለት ከእስር ከተፈቱት ከሁለቱ አንዷ ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ ነች የጋዜጠኛ መአዛ ባለቤት አቶ ሮቤል ገበየሁ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት “ላለፉት 23 ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስራ ቆይታ ዛሬ የዋስ መብቷ ተጠብቆ ተለቃለች” ብለዋል።

በተመሳሳይ ዜና ዛሬ ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ከተጠረጠረበት “ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት” ወንጀል በ10,000 ብር ዋስ ተለቆ ቤቱ መግባቱን ጠበቃው ታደለ ገ/መድህን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ሰኔ 10 ቀን በዋለው ችሎት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ መአዛ መሃመድ በ10 ሽህ ብር ዋስ ከእስር እንድትውጣ ወስኖ ነበር። ከዚህ ቀደም የፌደራል የመጀመሪያው ፍርድ ቤት በተመሳሳይ የጋዜጠኛዋ የዋስ መብት እንዲከበር የፈቀደ ቢሆንም፣ መርማሪ ፖሊስ ዋስትናውን ተቃውሞ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል።

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ “ሮሃ” ሚድያ የተሰኘ ዩትዩብ ቻናል መስራች እና ባለቤት ስትሆን ቅዳሜ ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከጓደኛዋ ቤት ፖሊስ “ለጥያቄ እንፈልግሻለን” ብሎ እንደያዛት የሚታወስ ነው።

የቀድሞ የኢትዩ ፎረም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ሃሙስ ግንቦት 18፣ 2014 ዓ. ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት ከተፈቱት ጋዜጠኞች መካከል ሰለሞን ሹምዬ ይገኝበታል። “ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን በ10 ሺህ ብር ዋስትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አርብ ሰኔ 10፤ 2014 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከእስር ተለቋል።

ሰለሞን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወጥቶ ከቤተሰቦቹ ጋር መቀላቀሉን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። ግንቦት 12፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ሰለሞን፤ ያለፉትን 28 ቀናት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ አሳልፏል።

በተመሳሳይም “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ፤ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ሃሙስ ሰኔ 9 ቀን ከእስር ተለቃለች። መስከረም ለ23 ቀናት በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ከሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስራ የቆየች ሲሆን ከእስር የተፈታችው ፖሊስ የተፈቀደላትን የዋስትና መብት በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው ይግባኝ ረቡዕ ሰኔ 8፤ 2014 ዓም ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.