ዜና፡ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጠና ሰላምና ልማት ላይ የሚሰራ አንተፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት (EFPD) የተሰኘ ድርጀት ወደ ስራ መግባቱን ገለፀ


ምስል- የፕረዘደንት ጽ/ቤት

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጠና ሰላምና ልማት ላይ የሚሰራ አንተፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት (EFPD) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የቅድመ ዝግጅት ሂደቱን በማጠናቀቅ  ትናንት ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢፌዲሪ ፕረዘደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዘዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ የቀድሞ ፕረዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሸመ፣ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ሚንስትሮች እና አንጋፋ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር  አካሄዷል፡፡

በኢትዮጵያና በኢጋድ አገራት በስፋት የሚስተዋሉ የሰላም እጦትና የደህንነት ስጋቶችን ብሎም ይህንን  ተከትሎ የተከሰቱ  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መስተጓጎሎችን በአግባብና በዘለቄታዊ ለመፍታት የችግሮቹ ዋንኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው የንግዱ ማህበረሰብ  በግንባር ቀደምነት በማሰለፍ  የተቋቋመው ይህ ድርጀት በአገሪቱ ሰላምና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ትኩረቱን  አድርጎ  ለመስራት ወደ ተግባር መግባቱ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተግልጿል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር በለጠ በላቸው በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ፎረሙ የንግዱ ማህበረሰብ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጠና የሰላምና ልማት ቀዳሚ ተዋናይ፣ አስተማሪና ጠበቃ የማድረግ፣ በአገራችንንና ኢጋድ  ቀጠና ዛላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ለመገንዝና የበኩሉን  አስተዋፆ ለማበርከት የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን የመቅረፅና መወሰን አቅም የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሆን ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢፌዲሪ ፕረዘደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአንድ ሀገር እድገት መሰረት ከሚሆኑት ሰላም፣ የኢኮኖሚ እድገትና ዲሞክራሲ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልፀው ለየትኛውም  ሀገርና ማህበረሰብ  የሰላም እጦት የሚመጣው ችግር ተዘርዝሮ ሊገለፅ የሚችል አይደለም ይህንንም እየኖርንበት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም  የሰው ልጅ ወጥቶ የሚገባው ሰርቶ የሚያፈራው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው ንግድ የሚካሄደው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ግጭትና የደህንነት ስጋት ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ፎረሙ መቋቋሙ አስፈላጊ ስለሆነ እገዛችን ይቀጥላል ሲሉ ገፀዋል፡፡

ፎረሙ የተመሰረተው የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድረጎ መሆኑን የገለፁት የድርጅቱ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ  ሰላምና ልማት ቁርኝት እንዳላቸው በመግለፅ “ስራ ፈጣሪው ባለሀብት በነበሩ በሰላም እጦት የደረሰባቸውን ጉዳት  እንዲሁም ሌሎች በኢንቨስትመንት ላይ  የተሰማሩ ባለሀብቶች ሰላም በደፈረሰበት ሁኔታ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው በተጨባጭ ያየን ስለሆነ  ሰላም ለልማት፣ ለህዝብ፣ ለሀገርና  ለባለሀብቱም አስፈላጊ በመሆኑ ሰላምን መሰረት አድርገን ለሀገራችን ልማትና ለህዝባችን የኑሮ ደረጃ እንዲመቻች ለማድረግ እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በተቀሰቀሱ የፀጥታ ችግሮች የንግዱ ማህበረሰብ ያረሰውን መሬት ሳይዘራበት፣ የዘራውን ሳያጭድ፣ ያመረተውንም ለገበያ ማቅረብ ሳይችል የሰውና ቁስ ሀብት እየወደመበት ይገኛል ያሉት የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ በላይነህ ክንዴ  “በሀገራችን  የሚሰሩ እጆች ሳይጠፉ በተለያየ ምክንያቶች ሰላማችንን ማረጋገጥ ባለመቻላችን  ሰርተን አገርና ወገን መለወጥ የምንችልበትን አቅም በከንቱ አባክነናል ካሁን በኃላ ግን የሀገሪቱን ሰላምና ልማት ለአደጋ ሲጋለጥ ዳር ከመቆም ይልቅ  እኛ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የመፍትሄው አካል ለመሆን ቆርጠን ተነስተናል” ብለዋል፡፡ አክለውም መንግስት የሰላምና የፀጥታ ችግሮች  በዘላቂነት እንዲወገዱ በሚደረገው ጥረት ጎን በመቆምና ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አንተፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት (EFPD) መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በቀድሞ ፕረዘዳንት ዶ/ር  ሙላቱ ተሾመ እና አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት ተቋቁሞ በኢትዮጵያና ኢጋድ ቀጠና ላይ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት ነው፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.