የደቡብ ክልል ዞኖች እና ወረዳዎች በጋራ በመሆን ሁለት ክልል ለመመስረት ውሳኔ አስተላለፉ




ምንጭ፡ ዊኪ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25 /2014 ዓ.ም፡- በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በመደራጀት ሁለት የተለያዩ ክልሎች ለመመስረት በየምክር ቤታቸው ውሳኔዎችን አሳለፉ።  የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 9ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን እና የስልጤ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 22ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልል አደረጃጀትን በተመለከተ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር አብሮ ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ  ሁለቱም ምክር ቤቶች አፅድቀዋል።

በዚህም መሰረት በአዲስ የክልል አደረጃጀት በጋራ ለሚደራጁ 11 መዋቅሮች ማለትም ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እና አማሮ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸው ተገልጿል።

የማዕከል ጉዳይ ሳይንሳዊ፣ ምክንያታዊ በሆነ እንዲሁም ውይይት ተደርጎበት በህዝብ ድምፅ የሚወሰን መሆኑን የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው የገለፁ ሲሆን  የክልል አደረጃጀት ጥያቄ የሕዝቡን ጥቅም ባስከበረ መልኩ እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መመልከቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀላባ፣ ሀዲያ ዞኖች እና  የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ከጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች ጋር በአንድ ላይ በመሆን አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት የስልጤ ዞን ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው 4ኛ ዙር 22ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ወስነዋል።  የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በመፍትሄነት በቀረበዉ መነሻ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብሎ መፀደቁ ነው የተገልፀው።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር የስልጤ፣ የጉራጌ፣ የሀዲያ፣ የካምባታ ጠምባሮ ፣ የሀለባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ካለቸዉ መልካም ምድራዊና ሥነ ልቦናዊ የጋራ መስተጋብር አንፃር በአንድ አደረጃጀት እንዲሆኑ የሚል የዉሳኔ ሀሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።

የዞን ምክር ቤቱ የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በመፍትሄነት የቀረበዉን መነሻ ሀሳብ ይኸውም ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ካምባታ ጠምባሮ ፣ ሀለባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ አንድ ላይ ይደራጁ የሚለዉን መነሻ የዉሳኔ ሀሳብ በአንድ ተቃዉሞ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎ አፅድቋል።

የደቡብ ክልል መንግስት ሰሞኑን የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችን “በሳል ውሳኔ” ሲል አድናቆት እና ምስጋና  አቅርቧል።ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ስር ተደራጅተው የነበሩት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል መስረተው ከክልሉ መውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን በደቡብ ክልል ያሉት አስራ አንዱም ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ባስተላለፉት ውሳኖዎች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሁለት ይከፈላል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.