ዜና፡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ለዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ



ምስል የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

ሐምሌ 27፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት  በሰቆጣ የሚገኘው  ክ/ጦር የቀጠናውን ሠላም በአስተማማኝ ከመጠበቅ ጎን ለጎን በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ለስሬል ቀበሌ አቅመ ደካማ እማወራና አባወራዎች አንድ መቶ ሀምሳ አንድ ሽህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

በቀጠናው የሚገኘው የዕዙ ዋና አዛዥ ድጋፉ  በተደረገበት ወቅት መገኘታቸውን ጠቅሶ፣ “ደጀን የሆነው  ማህበረሰባችን እንዳይቸገር ሠራዊቱ ካለው በማካፈል በጎ ተግባር አከናውኗል። ድጋፉም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት”  ሲሉ ማሳሰባቸውንም ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኦፊሴላዊ ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የክ/ጦሩ ዋና አዛዥ  በበኩላቸው “ያለ ህዝብ ምንም ነን” በሚል መርህ ክ/ጦሩ ለ40 አቅመ ደካሞች  ያደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የህዝባዊነቱ መገለጫ ነው ያሉ ሲሆን በቀጣይነትም አረም በማረምና ሰብል በመሠብሰብ የበጎ አድራጎት ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የስሬል ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ማርያሞ ሽምናትና አቶ ወልደኪዳን ተበጀ በሰጡት አስተያየት ሠራዊታችን የሠላማችን ምንጭ በመሆን ህይወቱን አሳልፎ መስጠቱ ሳያንሰው ለችግራችን ፈጥኖ በመድረስ ያደረገው የስንዴ፣ የዘይት፣ የአልባሳት እና ሌሎች ያደረጋቸው ድጋፎች ዘላቂ አብሮነቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ሃምሌ 5፣ 20141 ዓ.ም  በአዲስ ስታንዳርድ  ባቀረበችው የዜና ትንታኔ በዋግ ኽምራ ተፈናቃዮች ላይ ያለውን የጤና ችግር መዘገቧ ይታወሳል። በተለይ በአበርገሌ ወረዳ የወባ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና አጣዳፊ ትውከት በሽታ በመከሰቱ ለስምንት ሰዎች ሞት ምክኒያት መሆኑን አዲስ ስታንዳርድ የዞኑን ጤና ጥበቃ ቢሮ በመጥቀስ ሪፖርት አድርጋለች።

የተባበሩት መንግስታት ሀዚሁ ሃምሌ ወር መጀመሪያ  ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በቱርክ መንግስት በተገነባ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ በያዝነው አመት ሰኔ 22 ቀን በተደረገው ሁለገብ ኤጀንሲ ግምገማ ተፈናቃዮች በተጨናነቀ ሁኔታ እንደሚገኙ እና ከደረጃ በታች ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዳገኘ አመልክቷል።

ጣቢያው ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 3000 ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን በማስጠለል ላይ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ሲሰጥ የነበረው ዕርዳታም በቋሚነት ሲደረግ እንዳልነበረ  እና በቂም እንዳልሆነም ተጠቅሷል። ሪፖርቱ አክሎም “ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት የለም” ያለ ሲሆን  አንድ የገላ መታጠቢያ  ብሎክ ብቻ እንዳለ ጠቅሶ  የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንደሌለም ተናግሯል። በመጸዳጃ ቤት እጦት ምክንያት ሰዎች ክፍት በሆኑ ቦታዎች እየተጠቀሙ መሆኑን አንስቶ ሁኔታውን “የጤና ጠንቅ” ነው ብሎታል። በቂ መጠለያ ባለመኖሩ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ለጤና እና ለጥበቃ ስጋት ተጋልጠዋል ሲልም የተ.መ.ድ ሪፖርት አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) መስሪያ ቤት ሐምሌ 20፣ 2014 ዓ.ም የእርዳት እህል የጫኑ ከባድ መኪናዎች አማራ ክልል ወደማገኙ  አበርገሌ፣ ፃግብጂ፣ እና ዝቋላ ወረዳዎች ከአንድ አመት በላይ ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመግባት ላይ መሆናቸውን  አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧም ይታወሳል።

በአካባቢው የተከሰተው የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ከአደጋ ጊዜ በላይ ተደራሽ መሆን አለበት ያለው ድርጅቱ የህይወት አድን ምግብ የማጓጓዝ ሂደት ቀጣይነት መኖር እንዳለበት ማስገንዘቡም ይታወቃል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.