ዜና፡ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተመረቀ

ምንጭ: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት

ብሩክ አለሙ

አዲስ አበባ፡ግንቦት 22/2014 ዓ.ም- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና  መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገው የአብ ሜዲካል ሴንተር ትብብር  በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ስራው ተጠናቆ በዛሬው እለት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመረቀ። 

ማዕከሉ በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን ባሟላ አዲስ ህንፃ ላይ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት  በማህበራዊ ገፅ ያሰፈረው ሲሆን በጤናው ዘርፍ በተለይም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና በኩላሊት ህመም ለሚሰቃዮ ዜጎች ትልቅ እፎይታ የሚሆን እንዲሁም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ዜጎች ተስፋን የሚሰጥ እንሆነም መረጃው አክሎ ጠቅሷል። 

የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ቀድሞ በሁሉም በመንግሥት ሆስፒታሎች ይሰጥ ከነበረው አገልግሎት በአምስት እጥፍ  በማሳደግ በአንድ ቀን ለ90 ዜጎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል። 

”አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየሰራን ነው” ያለው የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊና ብቁ የጤና ተቋማት በመገንባት ተመጣጣኝና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎትን ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር “ ሰው በሚያውቀው በተማረበት በርካታ ድንቅ ስራ ሊሰራ እንደሚችል ዛሬ አይቻለሁ፤ ባየሁትም ነገር ተደስቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናሊዝም ጠፍቶ በመቆየቱ ምክንያት ማየት የሚገባንን ነገር ለብዙ ጊዜ ማየት ሳንችል ቆይተናል፡፡ በምንችለው በተማርነው ሁላችንም አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን” ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ ሲዋቀር ከተሰጡት ተልእኮ ውስጥ አንዱ የጤና ስራ ማስፋፋት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሆስፒታሎች ንፁህና ለሁሉም ሰው ተስማሚ መሆን አንዳለባቸው ገልፀው “ አሁን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየት ችያለው” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የኩላሊት ህመም የጤና ስርዓቱን እየፈተነ ያለ ህመም በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት አመታት ምንም ገቢ የሌላቸውን እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች ነፃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው በዚህም በሁለት አመታት ውስጥ 24 ሚሊየን ብር ያህል ድጎማ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ትልቁና ዘመናዊ የአይን ህክምና ማእከል ሆኖ እንዲወጣ በአዲሱ አመት ለህዝባችን አዲስ ምስራች እናበስራለን ያሉት ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን የጤና ማእከል ለማድረግ 24 ቦታዎችን ለግል ዘርፉ የሰጠ መሆኑንና አስተዳደሩ በራሱ አቅም ደግሞ ሶስት ሆስፒታሎችን በጀት መድቦ እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.