ዜና፡ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ሊቆጣጠረዉ የማይችለው አጠቃላይ ሃገራዊ ቀውስ ተፈጥሯል – ኦፌኮ

ዲስ አበባ፣ ህዳር 30/2015 ዓ/ም፦ ኦሮሚያ በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የሆነ የጦርነትና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፤ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ሊቆጣጠረዉ የማይችለው አጠቃላይ ሃገራዊ ቀውስ ተፈጥሯል ሲል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ።

ፓርቲው ትላንት ባወጣው መግለጫ በክልሉ በየቀኑ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፤ በሺህ የሚቆጠሩት ቤትና እርሻዎቻቸው እየወደመ ነው ብሏል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ በግጭትና በተፈጥሮ ድርቅ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ያለበቂ ድጋፍ ለረሃብና እርዛት መጋለጣቸውን ገልጧል፡፡

መግለጫዉ ከሰሞኑ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች የተከሰተዉንና ለባርካታ ሰዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነዉን በታጣቂዎች የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ የወጣ ነው።

ሌሎች የፖላቲካ ፓርቲዎች ቀደም ብለዉ በጉዳዩ መግለጫ ያወጡ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቀላሉ መድረስ በማይችሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦችን እንዲያስታጥቅ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ኦፌኮ በመግለጫው መንግስት የህዝብን ድህንነት ማስጠበቅ አለመቻሉን ጠቅሶ ከጎረቤት ክልል የሚነሱ፤ እንዲሁም ኦሮሚያ ውስጥ የተደራጁና የታጠቁ የፋኖና የአማራ ክልላዊ መንግስት ታጣቂዎች እንዲሁም በመንግስት አካላት የሚደገፉ ህገወጥ ሚሊሻዎች ህጻናት፤ ሴቶችና አዛውንቶች ላይ ጥቃት አየፈጸሙ ነው ያለ ሲሆን ለዚህም መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል። 

የታጠቁ ሀይሎች በክልሉ ሰበዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፅሙ፤ በህገመንግስቱ የተጣለበትን የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የሚወጣና ህዝቡ ለደህንነቱ የሚተማመንበት የመንግስት አካል አልተገኘም ብሏል ኦፌኮ በመግለጫው፡፡

መንግስት በክልሉ ያለዉን የፖለቲካ ቀዉስ ለመፍታት ወታደራዊ ዘዴን በመምረጡ ንፁሃናንን ለሞትና ለስቃይ ዳርጓል ያለዉ መግለጫዉ ይህ አካሄድ ቀውሱን ይበልጥ እንዲባባስና እንዲወሳሰብ ብሎም ወደ መላው የኦሮሚያ ክፍሎች እንዲስፋፋ አድርጎታል ብሏል።

በተጨማሪም ኦፌኮ የጸረ-አመፅ ስልቱ አካል የሆነውና ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ በሚያደርግ መንገድ እራሳቸውን እንዲከላከሉ በማለት ማነሳሳትና ማስታጠቅ መምረጡ፤ ከጎረቤት ክልል የተደራጁና የታጠቁ ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ ኦሮሚያ ውስጥ መጠነ ሰፊ እልቂትን የሚጋብዙ የእርስበርስ ግጭቶችን ያስከተሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ እያደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

ኦፌኮ በመግለጫው “ህዝቡን  “የሸኔ ደጋፊ፤ የሸኔ ቀላቢ ነው” በማለት በመከላከያ፤ በኦሮሚያ ልዩ ኃይልና በፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮኖች)፤ የገበያ ቦታ፤ የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያ መንደሮችን፤ ትምህርት ቤቶችን፤ የሃይማኖት ማምለኪያ ሥፍራዎች ጭምር ላይ ያለ ልዩነት ቦንብ እና ሮኬቶች እያዘነቡ ሰላማዊ ዜጎችን እየጨፈጨፉ ይገኛሉ” ብሏል፡፡

በኦሮሚያ ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይትና በድርድር የፖለቲካ እልባት እንዲያገኝ ጥረት መደረግ አለበት ሲልም ለተለያዩ አካላት ጥሪዉን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ቡድኖችና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ወቅቶች እርስ በእርሳቸው በሚያደርጓቸው ውጊያዎች፣ በሌላ ወቅት በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ሲቪል ሰዎች “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” ተብሎ ሊመደብ ለሚችል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መዳረጋቸዉን አስታዉቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.