ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ቡድኖችና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሚያደርጓቸው ውጊያዎች እንዲሁም በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች በርካታ ዜጎች ለ “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” ተዳርገዋል – ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/ 2015 ዓ.ም ፡- በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ቡድኖችና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ወቅቶች እርስ በእርሳቸው በሚያደርጓቸው ውጊያዎች፣ በሌላ ወቅት በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ሲቪል ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል፣  “አንዳንድ ቀበሌዎች ወይም የገጠር ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወይም በከፊል ወድመዋል” ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የደረሱ ግጭቶችና ጥቃቶች ያስከተሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” ተብሎ ሊመደብ የሚችል ስለመሆኑ በርካታ አመላካቾች መኖራቸውንም ኢሰመኮ አስታዉቋል።

ኮሚሽኑ ትላንት ባወጣው መግለጫ መሰረት ግጭቶችና ጥቃቶች የተፈፀሙት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በሰሜን ሸዋ፣ በቄለም ወለጋ ዞን፣ ኢሉ አባቦራ ዞን፣ በቡኖ በደሌ ዞን፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ ዞን እና በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በተለይም በኪረሙ፣ ጊዳ አያና፣ አልጌ፣ ሁሩሙ፣ በአሙሩ፣ ሆሮ ቡሉቅ፣ ጃርደጋ ጃርቴ፣ ቦሰት፣ ግንደበረት፣ ጮቢ፣ ደራ፣ ኩዩ፣ መርቲ ጀጁ እና የአርሲ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ጭምር ናቸው፡፡

በስድስት ውር ውስጥ ባደረገው ክትትል መሰረት በተለያዩ ወቅቶች በተዘረዘሩት አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም በመንግሥት “እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች”፣ ከሌሎች ክልሎች ጭምር እንደመጡና በተለምዶ በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የሚነገሩ የታጠቁ ቡድኖች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጫለው ብሏል።

ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር ወር 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በነዚህ ታጣቂ ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በብዙ መቶዎች የሚገመቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፣ ብዛታቸው የማይታወቅ ሰዎች ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚኖሩበት ቀዬ መፈናቀላቸውን አስታዉቋል።

ኮሚሽኑ ከታጣቂዎች በተጨማሪ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙና አንዱን ወይም ሌላኛውን “ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ” በሚል ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ተገቢ የሆነ ማጣራት ሳይደረግ ታጣቂ ቡድኖችን ኢላማ በማድረግ በሲቪል ሰዎች የመኖርያ ሰፈሮች አቅራቢያ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች፣ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስሮች፣ ተጠርጠሪዎችን የማሰቃየት ተግባራት በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም በተጠቀሱት አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታና የአስተዳደር አባላት መገደላቸውን፣  የመንግሥት እና የሲቪል ሰዎች ንብረቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም መውደማቸውን እና መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች ላይ ውደመት መድረሱን  ወይም መቋረጡን ገልጧል። አክሎም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያለ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወይም በቂ ባልሆነ አቅርቦት ምክንያት በከፍተኛ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም የሰብአዊ እርዳታና የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መዘግየት ወይም አለመኖር፣ እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ የሚቋረጡ መንገዶች፣ የምርት ሥራዎች፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ችግርና እንግልት የዳረጉ ናቸው፡፡

ሲቪል ሰዎች፣ እንዲሁም በአካባቢዎቹ ባለው ሁኔታ ሳቢያ ወደሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ሁሉንም ባለድርሻዎች ከማስተባበር ጀምሮ በቂ የፀጥታ ኃይል ማሰማራትና አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት በአፋጣኝ ማድረግ ይገባል ሲል ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

“አጠቃላይ ሰቆቃው ከዚህ የበለጠ ሊቀጥል ስለማይችል ሳይውል ሳያድር ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ሊደረግለት ይገባል” በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥቱ ተቀናጅተው በአፋጣኝና በሙሉ ትኩረት በመሥራት ዘላቂ ምላሽ መስጠት አለባቸውም ተብሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.