አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/ 2015 ዓ.ም፡- በምዕራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና እና ኪረሙ ወረዳዎች በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መሆናቸውን የአካባቢው ባለስልጣን እና ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ። ከ30,000 በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ያለ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ እና የህክምና አገልግሎት በጊዳ አያና ወረዳ ጊዳ ከተማ ሰፍረው ይገኛሉ።
የጊዳ አያና ወረዳ አስተዳዳሪ እጂጉ ጉደታ ከጊዳ አያና ወረዳ በርካታ መንደሮች ወደ 16,000 የሚገመቱ ተፈናቃች እንዲሁም ከኪረሙ ወረዳ ወደ 15,000 የሚገመቱ ተፈናቃዮች በጊዳ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ ብለዋል። አንዳንድ ነዋሪዎችም እስከ አምቦ ከተማና ሌሎች በአቅራቢያው ወዳሉ አካባቢዎች መሰደዳቸውንም አክለው ገልጸዋል።
“ተፈናቃዮቹ ልጆችን ጨምሮ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አዛውንቶች ይገኙበታል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንጀራ እና ውሃ እያቀረቡላቸው ቢሆንም መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላትም ሆነ ለመመገብ በፍፁም አይበቃም” ሲሉ ኢጂጉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
በኪራሙ ወረዳ ግጭት በመቀጠሉ የመንግስት የሰብአዊ አገልግሎት ሰጭዎች በአካባቢው መንቀሳቀስና መስራት አልቻሉም ብለዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለገ የጊዳ አያና ከተማ ነዋሪ፣ መንግስትም ሆነ የእርዳታ ድርጅቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ ማድረግ እንዳልቻሉ አረጋግጧል።
ነዋሪው አክሎም “የሚበሉት ሆነ የኪስ ገንዘብ ወይም መጠለያ የላቸውም። ከፊሎቹ በከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው የሰፈሩት፤ ሌሎቹ ደግሞ በሰዎች ቤት ናቸው። የውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አያገኙም። አብዛኛዎቹ ፍራሽ እና ልብስ የላቸውም” ሲል ገልጧል።
በተመሳሳይ መልኩ በኪረሙ ወረዳ የተፈፀመውን ጥቃት ሸሽተው የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር ከተማ የደረሱ ከ4,000 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ዶቸ ቨለ ዘግቧል። ነዋሪዎቹ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (በተለምዶ ሸኔ) እና በክልሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች የደረሰባቸውን ጥቃት በመሸሽ ከሶስት ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ ባህር ዳር መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እህታገኘሁ አደመ ተፈናቃዮቹ በኪራሙ ወረዳ የሚደርስባቸውን ጥቃት ሸሽተው ባለፈው ሳምንት ባህር ዳር መድረስ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አክለውም ከሶስት አውቶቡስ በላይ የሚሆኑትን ተፈናቃዮች ወደ ፍላቂትና ጃዊ እንዲሁም ወደ ላይ ጋይንት ሸኝተናል፣ አሁንም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአማራ ተወላጆች ወደ ክልላችን እገቡ ነው፣ ምዝገባዎችን አድርገን መኪናዎችን እያመቻቸን ዘመድ ያለው ወደ ዘመዱ እንዲሄድ ከአንድ ወር ቀለብ ጋር እንሸኛለን፣ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው ” ብለዋል፡፡
ህዳር 7 እና 20 በኪሪሙ ወረዳዎች ውስጥ በተፈፀሙ ሁለት ጥቃቶች እና የአከባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎች ከአጎራባት አማራ ክልል የፋኖ ታጣቂ ሃይልን በከሰሱበት ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ መላው የኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም ህዳር 24 እና 25 የፌደራል መንግስት እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች እና የታጠቁ የፋኖ ሚሊሻ ቡድኖች እና የኦሮሞ ነጻነት አባላትን ባሳተፈ ውጊያ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡
የፌደራልም ሆነ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል መንግስት ስለ ግጭቱ እስካሁን ያሉት ነገር የለም የለም።
ከሰኞ እለት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች በኦሮሞ ላይ ተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ጥቃቶች በማውገዝ እያካሄዱ ያለውን ተቃውሞ ቀጥሏል ።
እሮብ እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በወለጋ የተቀሰቀሰው ግጭት ሰላማዊ ዜጎችን ከቀያቸው እያፈናቀለና መሠረተ ልማቶችን እያወደመ መሆኑን ገልጿል። አክሎም አዲስ የተፈናቃዮች ቁጥር ገና አልተረጋገጡም ነገር ግን አሁን ባለው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
ድርጅቱ ህዳር 2 ይፋ ባደረገው ዘገባ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሰብአዊ ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ብሏል። በዘገባው መሰረት የችግሩ ዋንኛ መንስኤ የታጣቂዎች ግጭት ነው። ዘገባው በምዕራብ ኦሮሚያ ከአማራ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች 740,000 የሚገመቱ ተፈናቃዮች መሆራቸውን ይገልፃል።አስ