ዜና፡የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽነር በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ

አቶ ምትኩ ካሳ

አዲስ አበባ ፣ ሀምሌ 6 ፣2014 ዓም ፦ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ኮሚሽነሩ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው ዛሬ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በፌደራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው እንደገለጹት፥ ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኤልሻዳይ ከተሰኘ በጎ አድራጎት ማህበር ባለቤት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በመጠርጠራቸው ነው።

ይህ ኤልሻዳይ የተሰኘ ድርጅት በአዋሽ፣ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በእንጅባራ በመሳሰሉ አካባቢዎች ተፈናቃዮች በሌሉበት ተፈናቃዮች አሉ በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ የእርዳታ እህልና አልባሳት በመረከብ ሽጦ ለተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት መግዛቱ በምርምራ መረጋገጡን ነው ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ የተናገሩት።

ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ እንደነበረም ረዳት ኮሚሽነሩ ማብራራታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ምንጭ፡ ፋና ቢ ሲ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.