ቃለ-ምልልስ፡ “መንግስት ለውይይት በሩን መክፈት፣የሰራተኞችን ጥያቄ መመለስ እንደዚሁም የስራ ታክስን መቀነስ አለበት”- አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ፎቶ_ ከክምችት

 በሞላ ምትኩ @MollaAyenew

ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ገፅታ እየተቀየረ መምጣቲ ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ብዙ የኢንዱስትሪዎች እና የማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በመስፋፋታቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች የስራ እድል ተጠቃሚ ቢሆኑም  በሰራተኞች  አያያዝና መብት ዙሪያ የሚነሱ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ግን እሙን ነው፡፡ ሠራተኞቹ  በርካታ ቅሬታዎችን ያነሳሉ። በዋናነት በአሀሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሰራተኞች የከፋ ችግር ላይ ወድቀዋል።  በኤጄንሲዎች  አማክኝነት በተለያዩ ተቋማት የሚቀጠሩ ሰራተኞችም  የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ለሚሰሩት ስራ ተመጣጣኝ ክፊያ እያገኙ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ የአዲስ ስታንዳርዱ ሞላ ምትኩ እነዚህን እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን በመያዝ ከአቶ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዚዳንት ጋር ቆይታ አድረጓል፡፡ ሙሉ ቃለምልልሱ በሚከተለው መልክ ቀርቧል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ – ከየካቲት 24-25 /2015 ዓ.ም በነበረው ግዜ አንድ ቡድን መርተው ትግራይን መጎብኘትዎ ይታወቃል የጉዞው ዓላማ ምን ነበር?

አቶ ካሳሁን ፡ – የተጓዝነው ቡድን 21 ሰዎችን የያዘ  ነበር፡፡  እኔን ጨምሮ አራት ሰዎች ከኢሰማኮ ጽህፈት ቤት ሌሎቹ የተቀሩት ከዘጠኙ ፌዴሬሽን  ከሁለት መሰረታዎ ማህበራት ከመብራት ሃይል እና ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሸ ሆነን ነበር የሄድነው፡፡ የጉዞው ዓላማ እንደሚታወቀው ትግራይ በነበረው ጦርነት ምክንያት እዚያ ካሉ አባሎቻችን ጋር አልተገናኘንም ነበር ሁሉም እንደሚያውቀው የኢሰማኮ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኢዚያ አለ፡፡ እንደዚሁም ከ70 ሺ በላይ  አባላት በትግራይ አሉን አንደኛ ምን ላይ ነበሩ? ምን ደርሶባቸው ይሆናል? የሚለውን ለማየትና ለማወቅ ነው የሄድነው፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው እንዴት ነበር የሚለውንና ለማየት ነው የሄድነው፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  ትግራይ ቅድመ ጦርነት የነበረችበትን ሁኔታ ያውቁ ይሆናል ብየ አገምታለሁ፡፡ አሁን በጉብኝታችሁ ያያችሁት  ምንድን ነው?

አቶ ካሳሁን –   አዎ ከጦርነቱ በፊት እንግዲህ መቐለን እና አካባቢዋን እንደዚሁም  በዚያ የነበሩትን ፋብሪካዎች አውቃቸው ነበር፡፡በእርግጥ መቐለ ከተማ ውስጥ  ያን ያህል የከፋ ጉዳት አላየሁም፡፡ ከተማ ውስጥ የተወሰነ እንቅስቃሴ አለ የሚንቀሳቀሱ ባጃጆችም መኪኖችም  አሉ፡፡ በእርገጥ የነዳጅ እጥረት አለ፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ጦርነት ላይ ስለነበሩ ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ተጎድተዋል፡፡ በእርግጥ እኛ አንድ ቀን ብቻ ነበር እዚያ ያሳለፍነው በመሆኑም ተዘዋውረን ብዙ ነገሮችን ማየት አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ከመቐለ ወጣ ብለን ውቕሮ የሚባል ከተማ ሄደን ሁለት ፋብሪካዎችን አይተናል፡፡  አንደኛው የሸባ ሌዘር ሲሆን ሌላው ደግሞ የሰማያት እምነበረድ ፋብሪካ ነው፡፡

ሸባ ሌዘር በፊት 1 ሺህ 2 መቶ ሰራተኞች ነበሩት፡፡  በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሰራተኞች የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ተጠግኖ ሰራ ላይ ይውላል የሚል  ምንም አይነት ነገር የለውም፡፡ እያንዳንዱ ሲስተም በፈንጅ ስለተመታ ውስጥ ተገብቶ በፈንጅ ስለተመታ ስለሆነ አንድም ብሎን ተጠግኖ ስራ ላይ ይውላል የሚባል የለውም፡፡መቶ በመቶ ወድሟል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰራተኞቹን አልጠራንም ተበታትነው የት እንዳሉም አናውቅም ብለውናል፡፡የተወሰኑ ሰራተኞች የርሃብ አደጋ እንዳጠቃቸው  የነገሩን ሲሆን እኛ ያየናቸውም ያገኘናቸውም እርዳታ ካልተደረገላቸው በጣም ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑ አይተናል፡፡

ሸባ ሌዘር ማለት ከጦርነቱ በፊት የውጭ ምንዛሪ ለኢትዮጵያ የሚያስገኝ  የነበረ ተቋም ነበር፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ወደ ውጭ የሚልክ እና ለአገር ውስጥም የሚያቀርብ ተቋም ነበር፡፡ በጣም ዘመናዊ ፋብሪካ ነበር፡፡ እንደ ሃገር ሲናስበው ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የነበረ ድርጅት ነው በፈንጅ የወደመው፡፡  የነበሩት ሰራተኞች እያንዳንዳቸው በአማካይ አምስት ቤተሰብ ቢኖራቸው 6000 ሰዎች ከዚሁ ፋብሪካ በሚያገኙት ገቢ ይተዳደሩ ነበር፡፡ የእንዚህ ሁሉ ሰዎች ጉሮሮ ነው የተዘጋው፡፡

እምነበረድ ፋብሪካ ሰማያታም በተመሳሳይ መልኩ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ስራ ላይ የሚውል አንድም ብሎን አልቀረም፡፡ ክሬይን ሳይቀር ወደ መሬት ገብቶ  ጉድጓድ የሚቆፍረው በፈንጅ እንዲቆረጥ ተደርጓል፡፡ በዚህ ፋብሪካም ምንም ዓይነት ስራ ላይ የሚውል ነገር አልተገኘም፡፡ በጉድጓዱ የገባውን ለማወጣት ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ እንደገና ለማቋቋም እንኳን በሌላ ቦታ ካልሆነ በነበረበት ቦታ ማደራጀት አይቻልም፡፡ መቶ በመቶ ነው የወደመው፡፡ እስካሁን ለሁለት ዓመታት በጦርነት ተከበው ስለነበርና ጦርነቱም ቀጥሎ ስለነበር አጠቃላይ በትግራይ የሚገኙ ሰራተኞች ቤተሰቦቻቸው ጭምር ከፍተኛ  ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  የተቋማቱ እና የሰራተኞቹ  ሁኔታ በዚህ ደረጃ  ላይ ከሆነ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ ካሳሁን ፡ –  በቀጣይ ምን ይሁን የሚለው በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በእርግጥ እኛ ያየነው ሁለቱን ፋብሪካዎች ብቻ ነው፡፡ በቦታው የሰራተኛ ማህበራት ቅርንጫፍ አመራሮች እንደነገሩን አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካም መቶ በመቶ ወድሟል፡፡ የማህበሩ አባላት ከጉብኝት ማግስት በነበረን ስብሰባ እንዳብራሩልን ሌሎችም ሙሉ በሙሉ የወደሙ  ፋብሪካዎች አሉ፡፡  እስካሁን ባለው ሁኔታ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ  እና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ብቻ ናቸው በከፊል ስራ የጀመሩት፡፡

የሰራተኞቹ እጣ ፈንታ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ተቋማቸው ሙሉ በሙሉ የወደሙባቸው ነው፡፡  ሌላው ደግሞ ተቋማቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ስራ እየጀመሩ ያሉት ሰራተኞች ናቸው፡፡   ሙሉ በሙሉ በወደሙ ፋበሪካዎች የነበሩ ሰራተኞች እጣ ፈንታ የክልሉና የፌዴራል መንግስታት ተነጋገረው መፍትሄ ካልፈለጉ በስተቀር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እነዚህ ሰራተኞች በእርሻ ስራ እንዳይሰማሩ መሬት የላቸውም፡፡ እንዳይነግዱ የመነገጃ ቦታም ሆነ ገንዘብ የላቸውም፡፡ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት ማቆየት በጣም ከባድ ነው ፡፡ እነዚህ ሰራተኞች ከቤተሰቦቻቸው ልዩ ትኩረት ክትትልና ድጋፍ ከክልል እና ከፌዴራል መንግስት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ስራ እየጀመሩ ያሉ ፋበሪካዎች እና የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ግን ስራቸውን እየቀጠሉ ስለሆነ መልካም ሁኔታ ይኖራል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  የሰላም ስምምነቱ ተደርጎ ወደ ትግራይ የአየር በረራ  ከተጀመረ ቆይቷል፡፡  በህይወት ያሉ እና የሌሉ ሰራተኞች  እንደዚሁም እንደገና መጀመር የሚችሉና ሙሉ በሙሉ የወደሙ ተለይተዋል?

አቶ ካሳሁን ፡ –   አሁን ባየነው ብቻ ይሄን ያህል ወድሟል ይሄን ያህል ተመልሶ ወደ ስራ ይገባል የሚል ግምገማ ለማቅረብ የሚያስችለን አይደለም፡፡ ሁለቱን ፋብሪካዎች ካየንና ከአካባቢው የማህበራችን አባላትና ከክልሉ ንግድና እንዱስትሪ ከተወያየን በህዋላ እንደ ኢሰማኮ የወሰነው በክልሉ የወደሙ ፋበሪካዎችን ተጠግነው ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉትን በህይወት ያሉና የሌሉ ወይም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰራተኞች የሚያሳይ  ወጥ መረጃ  እንዲኖረን ጥናት ለማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የተጠቃለለ መረጃ አልያዝንም ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡

በትግራይ ያሉ ሰራተኞች አንድም በጦርነቱ የሞቱ የተጎዱ አለያም በርሃብ የተጎዱ እንዳሉ ሰምተናል ነገር ግን የተጠቃለለ መረጃ እንዲኖር በመላው ትግራይ ጥናቱን ለማድረግ ፕሮጀክት ሰርተን ለጥናቱ የሚያስፈልገንን  እንደ መኪና ነዳጅ ባለሙያ የመሳሰሉትን ለማሰማራት የሚያስችለን ገንዘብ ለማግኘት ፕሮጀክት አዘጋጅተን ድጋፍ ሰጪዎች ጋር እየተነጋገርንበት በመሆኑ በቅርቡ የሚንሰራው ይሆናል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  የሰራተኞች ደሞዝ አከፋፈል ጋር ተያይዞ  ያለው ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ካሳሁን ፡ – በትግራይ የሚገኙ ሰራተኞች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ  ለሁለት ዓመታት ያህል ደሞዝ አላገኙም፡፡ የራሳቸው ገንዘብ ኖሯቸው ቢሆን እንኳን የባንክ አግልግሎት ባለመኖሩ የተነሳ ገንዘባቸውን ማግኘት አይችሉም፡፡ ገንዘብ በጃቸው የነበራቸው እንኳን ቢኖረ አቅርቦት የሚባል ነገር ባለመኖሩ  ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለማንም ሰው የጉዳቱ ደረጃ መገመት አይከብድም፡፡በነበረው ጦርነት ምክንያት  ስራ የለም ደሞዝ የለም አቅርቦት የለም ከዚህ አንጻር ሰራተኞች ከፍተኛ መቦሳቆል ደርሶባቸዋል፡፡  በአሁኑ ወቅት እንደ ባንክ ቴሌ መብራት ሃይል የመሳሰሉ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ስራ በመጀመራቸው ደሞዝ መክፈል ጀምረዋል፡፡

….. ከሁመራ “ህይወት መካናይዘሽን እርሻ” እና “የወልቃይት ሱኳር ፋብሪካ” ሰራተኞች ሙሉ  በሙሉ ተፈናቅለው መቐለ መጠለያ ማዳበሪያ ዘርግተው እርዳታ እየጠበቁ ነው፡፡  ሙሉ ኑሯቸውን በፋብሪካዎቹ ላይ ስለነበረ አሁን ማረፊያ ቤት ስለሌላቸው ድናኳን ላይ ይገኛሉ

                                                                   አቶ ካሳሁን

አንዳንዶቹ ሶስት ወራት ያህል ተመልሰው የከፈሉ አሉ፡፡ እነዚህ ለወደፊቱም ተስፋ ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ያለፉት ሁለት ዓመታት የሰራተኞች ክፊያን በሚመለከት እስካሁን ገና የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር እቅድ  አለን፡፡ አሁን ትልቁ ችግር ሙሉ በሙሉ የወደሙ ተቋማት ሰራተኞች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ለዚህ መንግስት መፍተሄ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የክልል እና የፌዴራል መንግስታት በፍጥነት የስራ እድል መፍጠር አለባቸው፡፡  በከፊል የወደሙትን ፋብሪካዎች በፍጥነት ስራ ለማስጀመር የሚያስችል  ከባንክም ይሁን ሌላ ዘዴ በመጠቀም ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሁመራ “ህይወት መካናይዘሽን እርሻ” እና “የወልቃይት ሱኳር ፋብሪካ” ሰራተኞች ሙሉ  በሙሉ ተፈናቅለው መቐለ መጠለያ ማዳበሪያ ዘርግተው እርዳታ እየጠበቁ ነው፡፡  ሙሉ ኑሯቸውን በፋብሪካዎቹ ላይ ስለነበረ አሁን ማረፊያ ቤት ስለሌላቸው ድናኳን ላይ ይገኛሉ፡፡  እነዚህ ሰራተኞች ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ተፈናቅለው በድንኳን ተጠልለው በከፍተኛ ችግር ላይ ስለሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንግስት እነዚህንም መደገፍ ይኖርበታል፡፡

ኢሰማኮ ማቋቋሚያ የሚሆን ገንዘብ ለመደጎም የሚያስችል አቅም የለውም ነገር ግን ወደ ስራ መግባት የቻሉትን ተቋማት ሰራተኞች በተለያዩ የስነልቦና እና  ተዛማጅ ስልጠናዎችን በመስጠት  የማገዝ ተግባራትን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  በራሳችሁ ገንዘብ መደገፍ ባትችሉም የወደሙትን ተቋማት ማቋቋም  እና ሰራተኞች ለሁለት አስርት ወራት ያልተሰጣቸው ክፊያ እንዲያገኙ  የተበተኑ ሰራተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ መንግስታትም  ሆነ ድጋፍ ሰጪ አካላትን የመግፋትና የሰራተኞች መብት እንዲጠበቅ የማድረግ ተግባር መስራት አይኖርባችሁም ማለት ነው?

“….ሙሉ በሙሉ በወደሙ ተቋማት ይሰሩ ለነበሩ ሰራተኞች ግን ያለፈን ደሞዝ መክፈል ቀርቶ የቀጣይ  ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ የክልል እና የፌዴራል መንግስታት ችግሩ መፍትሄ የሚያገኝበትና እነዚህ ሰራተኞች የሚደገፉበትን መንገድ እንዲፈልጉ እንጠይቃለን ክትትልም እናደርጋለን”
                                                 አቶ ካሳሁን

አቶ ካሳሁን ፡ –  ይሄ ዋናው ስራችን ስለሆነ እንሰራለን፡፡ የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ውይይት እያደረግን መፈታት ያለበትን ችግር ለመፍታት እየሰራን ነው፡፡ ግን ከገንዘብ አንጻር ማህበር በመሆናችን የሚናደርገው ነገር አይኖርም ቀጥታ ፈንድ ማድረግ አንችልም፡፡ ማድረግ የሚችሉ እና ማድረግ ያለባቸውን ተቋማት እንዳልከው ክትትል በማድረግ እንዲፈጸም የማድረግ ስራ አጠናክረን የሚንቀጥልበት ይሆናል፡፡ ስራ በቀጠሉ ተቋማት ላሉ ሰራተኞች ውዝፍ ደሞዝ እንዲከፈል  ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራችንን እንቀጥላለን እንጠይቃለን፡፡ ሙሉ በሙሉ በወደሙ ተቋማት ይሰሩ ለነበሩ ሰራተኞች ግን ያለፈን ደሞዝ መክፈል ቀርቶ የቀጣይ  ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ የክልል እና የፌዴራል መንግስታት ችግሩ መፍትሄ የሚያገኝበትና እነዚህ ሰራተኞች የሚደገፉበትን መንገድ እንዲፈልጉ እንጠይቃለን ክትትልም እናደርጋለን፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  ከነበረው የፖለቲካ ጡዘት ጋር ተያይዞአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች  ለረጅም ዓመታት መስሪያ ቤት  የተባረሩ ሰራተኞች ጉዳይስ እንዴት ነው?

አቶ ካሳሁን ፡ –  በፋብሪካ ደረጃ ወይም በመንግስት የልማት ድርጅት ይሰሩ የነበሩ በወቅቱ ታስረው የነበሩ ሰራተኞች እንደተፈቱ በሙሉ ወደስራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡ በሲቪል ሰርቫንት ያሉት በኢሰማኮ የታቀፉ ባለመሆናቸው ለነሱ ለመጠየቅ አንችልም፡፡ ይህ በማህበራችን ስር የታቀፉ ባለመሆናቸውና የሚተዳደሩትም በሌላ መመሪያ በመሆኑ ነው፡፡ በኢሰማኮ ስር ባሉ ፋብሪካዎች እና የልማት ድርጅቶች ሲሰሩ የነበሩ ከስራ ተባረው የነበሩትን  ግን ሁሉንም በወቅቱ  እንዲመለሱ አድርገናል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  በኤጀንሲዎች አማካይነት  በተለያዩ ድርጅቶች የሚቀጠሩ ሰራተኞች ለሚሰሩት ስራ ተገቢውን ክፊያ እያገኙ እንዳልሆነ እና የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰባቸው መሆኑ ቅሬታ አለ፡፡  ማህበሩ ይህንን እንዴት ይመለከተዋል ምንስ እየሰራ ነው?

“….. የወጣው መመሪያ 20/80 የሚባል  ነው፡፡ 20 በመቶ ለአስተዳደራዊ ወጪ 80 በመቶ ደግሞ ለሰራተኛው የሚከፈል ነበር፡፡ ኤጄንሲዎች ይህንን ተግባራዊ አናደርግም በማለታቸው ፍርድ ቤት ላይ ክርክር ነበር፡፡ ክርክሩ እስከ ሰበር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ ሰበር በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠ በህዋላ አሁንም አፈጻጸም ላይ ችግር አለ” 
                                               አቶ ካሳሁን

አቶ ካሳሁን ፡ –  ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በ2011 ዓም አንድ መመሪያ ወጥቶ ነበር፡፡ በአዋጁ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያው ያወጣል በሚል ተጠቅሶ ስለነበር መመሪያ ወጥቷል፡፡ የወጣው መመሪያ 20/80 የሚባል  ነው፡፡ 20 በመቶ ለአስተዳደራዊ ወጪ 80 በመቶ ደግሞ ለሰራተኛው የሚከፈል ነበር፡፡ ኤጄንሲዎች ይህንን ተግባራዊ አናደርግም በማለታቸው ፍርድ ቤት ላይ ክርክር ነበር፡፡ ክርክሩ እስከ ሰበር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ ሰበር በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠ በህዋላ አሁንም አፈጻጸም ላይ ችግር አለ፡፡አፈጻጸም ላይ ችግር ስላለ የሚመለከተው ስራ እና ክህሎት ሚኒቴር ነው ይህ ጉዳይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ መሰረት እንዲፈጸም ለክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች  እንዲያስፈጸሙ አዲስ አበባን ጨምሮ ደብዳቤ ተጽፏል እንደዚያም ሆኖ አሁንም ችግሩ አልተፈታም፡፡ አሁንም ይሄ ነገር ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ስለዚህ አሁንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርንበት  ነው ያለነው በዚህ ጉዳይ ባለፈው ሳምንትም ስብሰባ ነበር መፈጸም እንዳለበት ተወያይተናል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  ይህ የሰራተኛ ጉልበት ብዝበዛ እየከፋ ነው የመጣው ስለዚህ ኢሰማኮ ደብዳቤ ተጽፎ እንዲሰራጭ ከማድረግ ባሻገር ለተፈጻሚነቱ ምን ጥረቶች አድርጓል?

አቶ ካሳሁን ፡ – የኤጀንሲ ቅጥርን በተመለከተ አሁን በዚህ ደረጃ ላይ ኤጀንሲዎች መቅጠር አይችሉም ለማለት ኦልረዲ አዋጅ አለ፡፡ ይሄ ምንድን ነው አዉትሶርስ የሚል ነው፡፡ ይሄ የመጣው መስሪያቤቶች ዋናው ስራቸው ላይ እንዲያተኩሩ  ከዋናው ምርት ውጭ የሆኑ ስራዎች ለሌላ ወገን አዉትሶርስ እንዲያደርጉ የሚል አዋጅ አለ፡፡

“…. አሁን ለምሳሌ በዚህ ስራ ላይ የሚሰራ ሰው  ከእያንዳንዱ ሰራተኛ በትንሹ 5 ሺህ የሚያገኝ ከሆነ  10 ሰው ቢቀጥር ይህ ኤጀንሲ 50 ሺህ ብር ቁጭ ብሎ በወር ያገኛል ማለት ነው ስለዚህ ሌላ ስራም አያስፈልገውም በቀላሉ ሃብት ያከማቻል ማለት ነው፡፡ብዙ ሰው ሲሆን ምን ያህል እንሚሆን መገመት ይቻላል”
                                                                አቶ ካሳሁን

በዚህ  መሰረት ደግሞ ኤጀንሲዎች ተቋቁመዋል የሚሰሩበት ደግሞ ራሱን የቻለ አዋጅም አለ መመሪያም አለ፡፡ አሁን ችግር የሆነው መቅጠራቸው ሳይሆን  የሚቀጥሩበት ዘዴ ነው ችግር የሆነው፡፡ የጉልበት ብዝበዛ የሆነው ምንድን ነው ለምሳሌ 10 ሺህ ውል ከገባው ድርጅት በአንድ ሰው ስም የሚወስድ ከሆነ ከሱ ላይ 7 ሺህ ይወስድና ወይ 3 ሺህ ይከፍለዋል ሌላውን እጀንሲው ለራሱ ይወስደዋል፡፡ ምንም ሳያመርት ምንም ሳያደርግ የአስተዳደሩን ስራ በመስራቱ ብቻ ይህንን ያደርጋል፡፡ይሄ የሰው ጉልበት ነው ጥንቃቄ ያስፈልጋል ኮሚሽን መውሰድ ሌላ ጉዳይ ነው ደሞዛቸውን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት  ለራስ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ በዚህ ስራ ላይ የሚሰራ ሰው  ከእያንዳንዱ ሰራተኛ በትንሹ 5 ሺህ የሚያገኝ ከሆነ  10 ሰው ቢቀጥር ይህ ኤጀንሲ 50 ሺህ ብር ቁጭ ብሎ በወር ያገኛል ማለት ነው ስለዚህ ሌላ ስራም አያስፈልገውም በቀላሉ ሃብት ያከማቻል ማለት ነው፡፡ብዙ ሰው ሲሆን ምን ያህል እንሚሆን መገመት ይቻላል፡፡  ስለዚህ ይሄ ብዝበዛ እንዲቆም 20/80 የሚል መመሪያ ነው እንዲወጣ ያደረግነው፡፡ በእርግጥ እነሱም ሰው ይቀጥራሉ ማኔጅ ያደርጋሉ ቢሮ ይከራያሉ ስራ ነው ስለዚህ ለእነዚህ አስተዳደራዊ ወጪዎች 20 በመቶ በውል ከሚያገኙት ይበቃል ለሰራተኛው ግን 80 በመቶው ለሰራተኛው ይከፈሉ ነው፡፡ይህንን አንከፍልም የሚለው ነው አሁን ችግር ሆኖ ያለው፡፡እኛ ከዚህ በፊት መስሪያ ቤቶች በራሳቸው እንዲቀጥሩ ስንከራከር ነበር፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ሲሻሻል ይሄ የኤጀንሲ ቅጥር ቀርቶ ድርጅቶች በራሳቸው ቢቀጥሩ ይሻላል  ይሄ የጉልበት ብዝበዛ እያመጣ ነው በእኛ አገር እየተሰራ ያለው ከሰለጠኑ አገራት በቀጥታ ተወስዶ ነው፡፡ የሰለጠኑት አገራት ሲስተም አላቸው ሁሉም ነገር መቆጣጠር ቀላል ነው የጠበቀ ህግ አላቸው ክትትል አላቸው ችግር የለም፡፡

እኛ አገር ክትትል የለም የጠበቀ የማስፈጸሚያ ህግ የለም የሚከታተለውም አካል ያን ያህል ጠንካራ አይደለም በዚህ ምክንያት ይህ ለኛ አገር በዚህ ሰዓት ጥሩ አይደለም ፡፡ ውጮቹ ይህንን የሚፈልጉት ለምንድን ነው አንደኛ  የሰው ሃይል እጥረት ይኖራል፡፡ ገበያ ወጥተው ሰው መቅጠር ግዜ ስለሚፈጅባቸው ሊያገኙም ስለማይችሉ ሌላ አካል እንዲሰራላቸው ያደርጋሉ፡፡ እኛ አገር ግን ማስታወቂያ ሲወጣ 10 ሰው ለመቅጠር ከ100 በላይ ነው የሚመዘገበው፡፡ ምንም የሰው ችግር በሌለበት እና በቂ የሰው ሃይ ባለበት  ለመቅጠር ያን ያህል ግዜ የሚወስድ ስላልሆነ አስፈላጊ አይደለም ብለን ስንከራከር አውትሶርስ ማድረግ በህግ የተቀመጠ ነው የአይ ኤል ኦ ህግም ነው የሚል ስለቀረበ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ መመሪያ ይውጣለት ሰራተኛው የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰበት ነው የሚል ሃሳብ ይዘን በመንቀሳቀሳችን 20/80 የሚለውን መመሪያ በወቅቱ በነበረው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲወጣ ተደርጎ ወደስራ ለማስገባት ጥረት ሲደረግ ኤጀንሲዎች ባለመስማማታቸው ተፈጻሚነቱ ሊራዘም ችሏል፡፡ አሁን ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ስለዚህ 20/80 የሚለው መመሪያ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቀጣይ ስራ ላይ እንዲውል ጥረት እናደርጋለን፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ – በእንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰሩ  ሰራተኞችም ከጉልበት ብዝበዛ በተጨማሪ ደሞዛቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ምን አየሰራ ነው?

አቶ ካሳሁን ፡ – ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በህግ እንዲወሰንና ሰራተኛው ጠጠቃሚ እንዲሆን እንቅስቃሴ የጀመርነው በ2011 ዓም ነበር፡፡ በአገራችን እንደጠቀስከው በእንዱስትሪ ፓርኮችም ሆነ በሌሎች ተቋማት ዝቅተኛ ደሞዝ ከ800 እስከ 1200 ድ ድረስ ነው፡፡ በዚህ ደሞዝ ሰው እንዴት መኖር ይችላል? በአገሪቱ ዝቅተኛ ደሞዝ ወለል የሚወስን ቦርድ መቋቋም እንዳለበት አዋጅ የወጣ ቢሆንም አዋጁ ከመወጣ በህዋለ በ2013 ዓም የቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ውይይት ተደርጎ ይታይናል ብለን ነበር ሆኖም ግን ምርጫ እና ጦርነት በአገሪቱ በመከሰቱ ምክንያት አልታየም ከዚየዓም በህዋላ ለስራና ክህሎት ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደዚሁም ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ አስገብተናል፡፡

“… በቅርበ ወደ ተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ እንዲቀጥል ለማድረግ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ  ኢሰማኮ መሄድ የሚችለው የመጨረሻ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅርበናል ሆኖም ግን እስካሁን መልስ አላገኘነም፡፡ ይህ ጉዳይ ምላሽ ካላገኘ ሁሉም ሰራተኛ እርዳታ ጠባቂ ይሆናል ማለት ነው”
                                                                            አቶ ካሳሁን

እስካሁን ድረስ ባለው ግዜ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲቆረጥ ያረብነው ጥያቅ መልስ ማግኘት አልቻልንም፡፡እስካሁን ድረስ ተወስኖ ስራ ላይ መዋል ነበረበት ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘንም፡፡  በመሆኑም አሁንም ውሳኔ እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኑሮ ሰማይ ነክቷል፡፡ 1200 ብር ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ አንድ ሰው በቀን አንድ ግዜ ሽሮ በልቶ ለመብላት በወር 1500 ብር ያስፈልገዋል፡፡ ሁሉን ነገር ትቶ ማለት ነው፡፡ ትራንስፖርት ልብስ ጤና እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ትቶ በቀን አንድ ግዜ መብላት እንኳን አይችልም፡፡ በአሁቡ ሰዓት አጠቃላይ ሰራተኛው ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቆ ነው ያለው፡፡ በአገራችን ከፍተኛ ደሞዝ የሚባለው 8000 እና 10000 ነው ፡፡ በአሁኑ ወቅት ጤፍ 8000 ገብቷል እበንግዲህ ሰው እንዴት ይኖራል፡፡

በመሆኑም ኢሰማኮ ግብር እንዲቀነስ ነው እየጠየቅን ያለነው፡፡ መንግስት ግን እንኳንስ ግብር ሊቀንስ ሰሞኑን ቫት እንደጨመረ ነው እየተነገረ ያለው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?  ኑሮ ውድነቱ ሰማይ ደርሷል ሰራተኛው ደሞዝ ግን እዚያው እንዳለ ነው፡፡ በቅርበ ወደ ተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ እንዲቀጥል ለማድረግ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ  ኢሰማኮ መሄድ የሚችለው የመጨረሻ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅርበናል ሆኖም ግን እስካሁን መልስ አላገኘነም፡፡ ይህ ጉዳይ ምላሽ ካላገኘ ሁሉም ሰራተኛ እርዳታ ጠባቂ ይሆናል ማለት ነው ስለዚህ መንግስት መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል በተለይ ግብር እንዲቀነስ ያቀረብነው ጥያቄ መልስ ካላገኘ በቅርቡ የኢሰማኮ ጠቅላላ ጉባኤ ይኖረናል ያን ግዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተን የሚንወስን ይሆናል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ – ኢሰማኮ አጠቃላይ የሰራተኞችን መብት ከማስከበር አንጻር የተገኙ ስኬቶች እና ያጋጠሙ ተግዳራቶችን ቢገልጹልን?

አቶ ካሳሁን ፡ –  አንዱ ስኬት ብለን የሚንወስደው ይሄ የኤጀንሲዎች ችግር ነው፡፡ይሄ ችግር በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አየታቀፉም ተብሎ መብታቸው እንዳይጠበቅ ተክልክሎ በሌላ አዋጅ ሲተዳደሩ ነበር፡፡ እንደ ሰራተኛ ተቆጥረው በአሰሪና ሰራተኛ አይታቀፉም ነበር ከ2011 ዓም በፊት፡፡ ከዚህ በፊት አዋጁ እንዲሻሻል የጠየቅንበት እና ወደ አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እንዲገቡ ትልቅ ትግል ስናደርግ የነበርነው ከእነሱም ጭምር ሆነን በ2011 ዓም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እንደሰራተኛ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ወደዚህ አዋጅ ከገቡ በህዋላ ደግሞ የደሞዝን ጉዳይ

ከአቅም አንጻር ከአሰሪው  ጋር መደራደር ስለማይችሉ የሰብአዊ መብት ጉዳይነም ስለሆነ መመሪያ ሊወጣለት ይገባል 2011 ዓም አዋጁ ከወጣ በህዋላ ስንታገል ነበር እንደገና ለዚህ መመሪያ ወጥቶ እራሳቸው ኤጀንሲዎች አሁን ባሉበት ሌሎችም በተገኙበት ውይይት ተደደርጎ ነው መመሪያው በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲወጣ የተደረገው፡፡ ይሄ 20/80 የሚለው መመሪያ በቀላሉ የመጣ አይደለም በከፍተኛ ትግል እና ድርድር ነው የመጣው፡፡ ወደ ተግባር ልንገባ ስንል ደግሞ  ኤጀንሲዎቹ አይሆንም ከሰራተኛው ጋር በስምምነት ነው የሚንሰራው  በሚል እንዳይደጸም ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይሄኮ እንደሌላ ምርት አይደለም የሚሰሩት ነገር የለም የሚያመርቱት ነገር የለም ሰውን ነው ማኔጅ የሚያደርጉት ይሄ ደግሞ የሰብአዊ መብት ኤሌመንት አለበት፡፡

የ20/80 አዋጅ አንዱ ስኬት አድርገን እንወስደዋለን፡፡ በ2011 ዓም እንዲሻሻል የተደረገው አዋጅ አሁን ባለበት ደረጃ አልነበረም ቀርቦ የነበረው፡፡ እንዲወጣ ተወስኖ የነበረ አዋጅ ሰራተኛውን ወደ ችግር የሚከተው ነበር፡፡በምንም ምክንያት ቢሆን አንድ ቀን ከስራ ከቀረህ ትባረራለህ፡፡ በወር ሁለት ቀን ካረፈድክ ከስራ ትባረራለህ፡፡ በዚህ ታክሲ መጨናነቅ ትራንስፖርት በሌለበት አገር 10 ደቂቃም አርፍድ 30 ደቂቃም አርፊድ ሁለት ቀን ክረፈድክ ከስራ ትባረራለህ ማለት ነው በዚያ አዋጅ መሰረት፡፡ የዓመት እረፍት ሰባት ቀናት ብቻ ነበር ተብሎ የነበረው  ብዙ ነገሮች ናቸው እዚያ ላይ ተቀምጠው የነበሩት፡፡ ያ አዋጅ እንዲቀየር ለማድረግ አጠቃላይ ሰራተኛውን አንቀሳቅሰን ለመንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ቀጥሎ ስራ ለማቆም ማስጠንቀቂያ ሰጥተንነው አዋጁ ወደ ውይይት ተመልሶ እንደገና የታየው፡፡ ውይይት ላይ ገባን በዚያ መካከል የመንግስት ለውጥ መጣ፡፡ ከቆምንበት ወደፊት በመሄድ ችግሮቹ እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡

ሌላ አንዱ ትልቅ በኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ህግ ውስጥ  የዝቅተኛ ደሞዝ ወለልገብቶ አያውቅም፡፡ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በህግ ውስጥ እንዲካተት ስንጮህ ቆይተን ለስንት ዓመታት ሲንደራደር ቆይተን በ2011 ነው የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ እያየ ዝቅተኛ ደሞዝ የሚወስን የደሞዝ ቦርድ ይቋቋማል የሚል በአዋጅ ተካቷል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ነው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ይህንን ይዞ የወጣው፡፡ ይህንን አድርገናል እንደሚታወቀው ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በአገራችን በተለያዩ ተቋማትና በእንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ሰራተኞች ዛሬ የሚከፈላቸው ከ800 እስከ 1200 ነው፡፡ሰው በዚህ ሰዓት እንዴት ብሎ በህይወት መኖር ይችላል፡፡ይሄ መወሰን ነበረበት እስካሁን ቦርዱ ቶሎ እንዲቋቋም የሚል ጠይቀን ነበር የመቋቋሚያ ደንቡ ላይ በ2013 ዓም እየተወያየን እያለን ኮቪድ መጣ ምርጫም ደረሰ ከዚያም ጦርነት መጣ፡፡ ይታይልናል ብለን ጠበቅን እስካሁን አልታየም በእኛ በኩል ለሚመለከታቸው ስራና ክህሎት ሚኒስቴር በአካል በማናገር ደብዳቤ በመጻፍ ሞክረናል በተለያየ ግዜም መግለጫ አውጥተናል አሁን መጨረሻ ላይ ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ለስራና ክህሎት ሚኒስቴር እንደዚሁም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በደብዳቤ ጠይቀናል፡፡አሁንም ምላሽ አላገኘንም ምላሽ እየጠበቅን ነው ያለነው፡፡ እስካሁን ቦርዱ ተቋቁሞ ዝቅተኛ ደሞዝ ወለል መወሰን ነበረበት፡፡ምንም እንኳን ከመጀመሪያ አንስቶ ዝቅተኛ ቢሆንም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ነዳጅ ጨምሯል ትራንስፖርት ቸምሯል ሁሉም ነገር ጨምሯል በዚህ ገንዘብ አዲስ አበባም ሆነ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ራሱን መግቦ መኖር አይችልም፡፡ ሌላው ነገር ሁሉ ትተነው ዝቅተኛ ቤት  አንድ ሽሮ ለመመገብ 50 ብር ነው፡፡ ይህ በወር 1500 ብር ነው፡፡ ሁሉን ነገር ልብሱን ስለሚጠጣው ውሃ ስለጤናው ትተን በቀን አንድ ግዜ ብቻ አን ሽሮ ከበላ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በተለይም አሁን አሁን ኑሮው እየከበዳ በመምጣቱ የሰራተኛ ደሞዝ ግን ባለበት መሆኑ ከፍተኛ ችግር ላይ ሰራተኛው እየወደቀ በመሆኑ የስራ ግብር ይቀነስልን ተርበናል በሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ያቀረብነው ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለማግኘቱ የሰራተኛው ስቃይ ቀጥሏል ማለት ነው፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ –  በጣም አመሰግናለሁ በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

አቶ ካሳሁን ፡ –  በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የሚፈልገው መልእክትመንግስት ሰራተኛውን ቢያወያይ መልካም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሰራተኛውን የሚያ አካል የለም፡፡ ሰራተኛው ከፍተኛ የሆነ የመደራጀትና የኑሮ ችግር እየደረሰበት ነው፡፡ መንግስት ሰራተኛውን ሊያወያይ ችግሩን ሊፈታ ይገባል፡፡ ሰራተኛውን ማግለል የለበትም፡፡ ሊንገለል አይገባም በሪ ሊዘጋብን አይገባም፡፡ መንግስት በሩን ለውይይት ክፍት አድርጎ ሰራተኛው ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.