ጥልቅ-ትንታኔ፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት መርማሪ ቡድን እሰጣገባ፤ ፍራቻ የተላበሰ የፖለቲካ ውሳኔ ወይስ ሉአላዊነት ?

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/ 2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሪፖርት አቅርቧል። በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው አባል ሀገራቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ምክር ቤቱ መርማሪ ኮሚሽኑን ካቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው እና ምንም አይነት ድጋፍ እንደማታደርግለት ስትገልጽ ቆይታለች፤ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል የተቋቋመ ነው በሚል ተችታዋለች።  

ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች እና አጋጣሚዎችን በመጠቀም መርማሪ ቡድኑ ስራው እንዲቋረጥ መጣሯን የተመለከቱ በርካታ ዘገባዎች ወጥተዋል። በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድረጅት የሰብአዊ መብት አመታዊ ጉባኤም ላይ መንግስት ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳዩ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል።

ከአንድ ወር በፊት ሮይተርስ የዜና ወኪል ይዞት የወጣው ዘገባ እንዳመላከተው የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ሰብአዊ ወንጀሎችን ለማጣራት የሚካሄደው ምርመራ እንዲቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት ማሰራጨቱን አስታውቋል። እርምጃውም የምርመራው ውጤት ይፋ እንዳይወጣ እና በምክር ቤቱም ለክርክር እንዳይቀርብ ሊያግድ የሚችል መሆኑንም አመላክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ከስልሳ በላይ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጭምር የተሳተፉበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ ስልጣን እና ተግባሩ እንዲቋረጥ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀርበውን ሃሳብ ውድቅ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ከስልሳ በላይ ከፈረሙት መካከል በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ሁለት የሰብአዊ መብት ተቋማት ብቻ ተሳትፈዋል። የትግራይ ዩኒቨርስቲዎች እና ሙሁራን ህብረትን ጨምሮ በትግራይ ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት ጥምረት በጋራ በመሆን መግለጫ በማውጣት መርማሪ ቡድኑን ደግፈዋል። የአዲስ ስታንዳርድ ምንጮች በሀገሪቱ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እንዲቀላቀሉ ጥሪ እንደቀረበላቸው ገልጸውልናል። ፊርማቸውን አኑረው ምልሻ የሰጡት ግን ሁለት ብቻ ናቸው፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ እና የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)።

ሌሎቹ ለምን አልተሳተፉም ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የህግ ባለሞያ እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም አገር ውስጥ ያሉት ሲቪል ማህበራት ቮካል ሁነው የማይወጡት መንግስት በጉዳዩ ላይ የያዘው አቋም ፖለቲካዊ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ የራሳቸውን አቋም በመርህ ተመርኩዘው ቢሰጡ የሚደርስባቸውን ያውቁታል ስለዚህ ለህልውናቸው ሲሉ ዝምታን መርጠዋል ብየ ነው የማምነው ብለዋል።

የትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ጥናት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበራቱ የተቋቋሙበትን አላማ ስተው የመንግስት እና የቡድኖች መሳሪያ በመሆናቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል። በቅርቡ ተቋማቱ በመቀለ ጉብኝት አድርገው እንደነበር የገለጹልን ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ የመጀመሪያው የቀረበላቸው ጥያቄ ሁለት አመት ሙሉ የት ነበራችሁ? ፖለቲካውን ተዉትና የተጎዳውን ሲቪል ማህበረሰብ አስባችሁ እንዴት ድምጽ አላሰማችሁም የሚል እንደነበር አስታውቀዋል። ሲጀመር ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይምጣ ማለት ያልደፈረ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ምን አንደበት ኑሮት ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል ሲሉ ተችተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት ለኢትዮጵያ 364 ተቋማት ያቀፈ ነው፤ ተቋማቱ በሰብአዊ መብት፣ በሰላም ግንባታ እና በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚሰሩ ናቸው፤ የጥምረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረንስ ፎር ዴሞክራሲ (ቪኢኮድ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ደርሰህ ምንም አይነት ጥሪ አልደረሰንም ሲሉ አስተባብለዋል። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ የሀገር ሉአላዊነት ይቀድማል፤ እንደፈለጉ እንዲገቡና እንዲወጡ መንግስት አለመፍቀዱ ትክክል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ማንም ይሁን ማንም በህግ ያጠፋ ሰው በህግ መጠየቅ አለበት የሚል እምነት አለን ያሉት አቶ ታደለ የህግ የበላይነት መከበር አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ተጠያቂነትን ለማስፈን ግን ሉአላዊነትን ያከበረ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኩል በጋራ የተሰራው ሪፖርት በቂ ካልሆነ ከነ አሳማኝ ምክንያቱ ቀርቦ በይፋ ግልጽ መደረግ አለበት፤ በመሆኑም ተመድ ውስጥ እርስ በርሳቸው እየተነጋገሩ ደስ ሲላቸው የሚያጸድቁ፣ ደስ ሲላቸው የሚሽሩ ከሆነ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ሃይሉ ለምን እንደተሳተፉ ጠይቀናቸው በሰጡን የኢሜይል ምላሽ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያልተደረሱ ቦታዎች ድረስ ሂዶ ለመስራት ይችላል ብለን እናምናለን ሲሉ ገልጸው ይህም እጅግ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ምን ያክል የሰው ህይወት እንዳስከፈለን ለማወቅ ገለልተኛ የሆነ መርማሪ በቦታው ሲመደቡ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።  ለተጠቂዎች እና ከጥቃቱ ለተረፉ ሰዎች እውነቱ ተመርምሮ መውጣቱ አስፈላጊ ነው፤ ጥቃቱ ፈጻሚዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለምን እንዳይመረምሩ ፈለገ ?

የህግ ባለሞያ እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም አለም አቀፍ መርማሪ ቡድን የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲመረምር መፍቀድ አጥፊዎች በመንግስት በኩልም ይሁን ማንም በየትኛውም የአለም ክፍል በተለይም በከፍተኛ የፍርድ ሂደቶች የመታየት እድሉን ከፍ ስለሚያደርገው ይመስለኛል እንዲመረምር በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፍላጎት የሌለው ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።

የታሪክ ተመራማሪው አቶ ፀጋዘአብ ካሳ በበኩላቸው የተፈጸመው ሰብአዊ መብት ጥሰት በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይንም የዘር ማጥፋት መሆኑን የሚያሳይ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት የሚኖረው የተጣራ ሪፖርት ከወጣ ማንኛውም ሰው በየትኛውም ሀገር አጥፊዎችን የመክሰስ እድል ይሰጠዋል ሲሉ ገልጸዋል። ይህም በተለይ በመንግስት በኩል ያሉ አጥፊዎች በሄዱበት እንዲሳደዱ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ በበኩላቸው በጦርነቱ በተለይ በትግራይ የነበረው የተለየ ባህሪ ነበረው ሲሉ ገልጸው ከኤርትራ እና ሶማሊያ ወታደሮች በተጨማሪ በአለማችን ላይ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ ሀገራት በጋራ የተሳተፉበት ሁኔታ ሁሉንም ነገር አወሳስቦታል ብለዋል። ይህንንም ሲያብራሩ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬት እና ኢራን በጋራ፣ ፈረንሳይ እና ቻይናም እንዲሁ አንድ ላይ በጦርነቱ ተሳትፏቸው አለ፤ በጦርነቱ ምክንያት በህዝቡ ላይ የተፈጸመው ግፍ በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የማይታሰብ ነው፤ ይህን ሁሉ ጉድ ይዘን ገለልተኛ መርማሪ ሲያጣራው የሚወጣው እውነት አስደንጋጭ ነው የሚሆነው ሲሉ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ከዚህ ሁሉ ጉድ በስተጀርባ ዋነኛው አስተባባሪ የፌደራል መንግስቱ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል ሲሉ የጠቆሙት የማነ ዘርአይ የመርማሪ ቡድኑ እንዳይሰራ፣ እንዳይመረምር ማድረጉ አይደንቅም፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በያዝነው አመት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የመርማሪ ቡድኑ ስራ ሀገሪቱ ለጀመረችው የሽግግር ፍትህ እንቅፋት ይሆናል ሲሉ ገልጸው ነበር።

አጣሪ ኮሚሽኑ የሚያደርገው ምርመራ ከሽግግር ፍትሁን የሚጎዳበት ወይምን እንቅፋት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም የሚሉት አቶ ያሬድ በሽግግር ፍትሁ አጥፊዎቹን ለፍርድ ለማቅረብ ለመንግስት ይጠቅመዋል ሲሉ ገልጸዋል። የሽግግር ፍትሁን ይደግፋል፤ ከዚህ ድጋፍ ውጭ እንደ ህግ ባለሞያ የሚያደናቅፍበት ምንም ነገር አይታየኝም ሲሉ ተናግረዋል። ተፋላሚ የነበሩ ሀይሎች አሁንም ማዶ እና ማዶ ያሉበት ሀገር ስለሆነ ገለልተኛ የሆነ በሁሉም የሚታመን ሀገር በቀል ይሁን ከውጭም ይምጣ ኢንኳየሪ ኮሚሽን ያስፈልጋል ሲሉ የገለጹልን አቶ ያሬድ በደሉ ሰፊ ስለሆነ ያንን አጣርተህ የበደሉ መጠን የወንጀሉ መጠን በአግባቡ ዶክመንት ካደረግህ በኋላ ነው ወደ ሽግግር ፍትህ የሚኬደው ብለዋል።

ሮይተርስ ትላንት ይዞት በወጣው መረጅ ግን ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን እንዲበተን የጀመረችውን ጥረት ማቋረጧን ዲፕሎማቶችንና የሰብዓዊ መብት ምንጮች ነግረውኛል ሲል ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ ጥረቱን ያቋረጠው፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ የጊዜ ቆይታ ከመስከረም በኋላ እንደማይራዘም ከምዕራባዊያን አገራት ጋር መግባባት ላይ በመድረሱ ነው ተብሏል፡፡

ምን አይነት የሽግግር ፍትህ ?

የሽግግር ሂደቱ ገና አልተጀመረም ሲሉ የገለጹልን አቶ ያሬድ በወሬ እና ወረቀት ላይ ነው፣ የምክክር መድረክ ላይ ነው ገና፣ በመንግስት በኩል ገና ግልጽ የሆነ አቋም ተወስዶ የተጀመረ ሂደት አለመኖሩን አስታውቀዋል። አሁን ውይይት እና ምክክር ነው እየተካሄደ ነው ያለው፤ መንግስት እኔ እንደዚህ አይነት የሽግግር ፍትህ ነው የማካሂደው ብሎ ይፋ አድርጎ ፖሊሲ ቀርጾ የጀመረው ስራ የለም ስለዚህ ለዚህ ነው መንግስት የትኛውን ነው የመረጠው የሚለው ወሳኝነት ያለው፤ ይሄ ማለት የተጠያቂነት ጉዳይ ለማውጣት የመመርመሩን ጉዳይ ለማምጣት ይወስነዋል ብለዋል።  

መንግስት በሚከተለው የሽግግር ፍትህ ዙሪያ የጠየቅናቸው አቶ የማነ ዘርአይ ፍትህ ሲባል ተጠያቂነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ሲሉ አመላክተው የፍትህ የመጀመሪያ ደረጃው ሃቅን መለየት ነው፤ ቀጥሎ ይቅርታ ነው፣ ቀጥሎ እርቅ ነው፣ ቀጥሎ ካሳ ነው ሲሉ አብራርተዋል። የሽግግር ፍትህ በጣም ያስፈልገናል ያሉት አቶ የማነ የሽግግር ፍትህን ለማምጣት ግን ዋነኛው ተግባር እውነቱን ማውጣት ነው፤ እውነት እንዲወጣ ደግሞ ገለልተኛ ምርምራ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል። እውነቱ እንዲወጣ እራሳችን እንደምንጥረው ሁሉ ሌሎች ሲመጡ ደግሞ ይግቡ ያግዙን ከማለት ይልቅ መከልከል አይገባም ብለዋል።

መርማሪ ከልክለህ፣ ሚዲያ እንዳይገቡ አድርገህ የሚመጣ የሽግግር ፍትህ አይታየኝም ሲሉ የተናገሩት አቶ የማነ ምን አይነት እውነት እንደሚወጣ እንደተፈለገ አልገባኝም ብለዋል። የትግራይን ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው የሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ለማየት መሞከር ትክክል አይደለም ያሉት አቶ የማነ የውጭ ሀይሎችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት የተካፈሉበት በአይነቱ ለየት ያለ ጦርነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

ስልጣን ላይ ያለው አካል ስልጣኑ በመጠቀም የሽግግር ፍትህ በሚል እያቀረበው ያለው ህጋዊነት ሊያላብሰው ይችላል ሲሉ ገልጸው ፍትሃዊነት ግን ሊያሰጠው አይችልም፤ አፓርታይድ በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ህጋዊ ነበር ህጋዊነቱ ፍትሃዊነትን አላላበሰውም ብለዋል።

መንግስት ስላቀረበው የሽግግር ፍትህ የጠየቅናቸው አቶ ያሬድ በሰጡን ምላሽ የሽግግር ፍትህ የተለያዩ ባህርያት አሉት መንግስት የመረጠው የትኛውን ነው የሚለው ጉዳይ ገና አለየለትም ሲሉ አስታውቀው በወንጀል ክስ ላይ መሰረት ያደረገ፣ አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ አድርጎ፣ እርቅ አውርዶ፣ ለተጎዱ ወገኖች ካሳ ሰጥቶ የሚያልፍ የሽግግር ፍትህ ሂደት አለ ብለዋል። ቀጥለውም “ሌላኛው ደግሞ የወንጀሉን ኢለመንት፣ የክሱን ሂደት ወደጎን አድርጎ በእርቅና ይቅር ይቅር በመባባል የሚካሄድ የሽግግር ፍትህ ሂደት አለ። መንግስት የተጠያቂነትን ጉዳይ ወደጎን ማድረግ ከፈለገ የማጣራቱ ነገር በሌላ የውጭ አካልም ቢሆን ላያስፈልግ ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከደረሰው ጉዳት አንጻር እንዲሁም ለሽግግር መንግስቱ ሂደት ሲባል ተጠያቂነትን ለማምጣት ዶክመንቶች በቅጡ መደራጀት እና መጣራት አለባቸው” በማለት አክለዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን ውጭ ሌላ አማራጭ አለ ወይ ?

የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ በመሆኑ አጣሪ ኮሚሽኑ ያስፈልጋል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ያሉን አቶ ያሬድ መንግስት ከዚህ በፊት ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በፈቀደበት መንገድ ማለትም በጋራ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር እንዲሰራ መፍቀድ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ እንደአማራጭ አቅርበዋል። ከፍተኛ ልምድ ያለው በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ መርማሪ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ቢያጣራ እንደ ሀገርም ጠቀሜታው ትልቅ ነው ብለዋል።

የትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ጥናት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ በዚህ አይስማሙም፤ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በጋራ ጥናት አድርገው ችግሮች በመፈጠራቸው ነው ይሄኛው ቡድን የተቋቋመው ሲሉ ይገልጻሉ። ከሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር እንዲሰራ ማድረግ አሁንም ለተጨማሪ የቀዶ ጥገና አይነት መፍትሄ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም ሲሉ ገልጸዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.