ዜና፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከሽብርተኝነት በመሰረዙ ለጊዜያዊ አስተዳደር ፈጥኖ መመስረትና ስራውን ማከናወን ወሳኝ ነው: ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል

ፎቶ ከፋይል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14/ 2015 ዓ.ም – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ ጊዜያዊ አስተዳደር ፈጥኖ ስራውን ማከናው እንዲችል ወሳኝ መሆኑ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ሊቀመንበሩ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ህወሓት ከሽብርተኝነት ከተነሳ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ተደንግጓል በዚህም ሠሰረት ዛሬ ድርጅታችን ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር በመሰረዙ ግዜያዊ አስተዳደራችን ስራ የሚጀምርበት፣ ሁኔታዎች ተሟልቷል ብለዋል።

በፌደራል መንግስቱ እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል በጀት በማዘጋጀት፣ የወንጀል ክሶች መነሳት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እና ግንኙነት መጀመሩንም ዶ/ር ደብረጺዮን ተናግረዋል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደራችን የተለማቸው ግቦቹ እንዲሳኩ በእኛ ወገን ሁሉንም አቅማችንን በማስተሳሰር እንረባረባለን ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን ሁሉም የትግራይ አቅም ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለመደገፍ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩን አወቃቀር በተመለከተም ከሰራዊቱ እና ከሙሁራን በተጨማሪ አሁን ባለው ሁኔታ በግዜያዊ አስተዳደሩ የተካተቱ ፓርቲዎች ህወሓት እና ባይቶና መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማወቀር ረገድ ከፍተኛ ተጽእኖዎች እንደነበሩ ያመላከቱት ሊቀመንበሩ በተለይ በህወሓት ላይ የነበረው የበረታ ቢሆንም የህዝብን ችግር በማስቀደም እንዲታለፍ ተደርጓል ብለዋል።

አሁን ያለንበት ግዜ የትግራይን እና የህዝቦቿን መጻኢ ሁኔታ የሚወስን ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን በአሁኑ ወቅት ወራሪዎች ከትግራይ ያልወጡበት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ባልተመለሱበት፣ ወንጀለኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ ባልተቀየሰበት፣ ህዝባችን ወደ መደበኛ ህይወቱ ባልተመለሰበት፣ የመልሶ ግንባታ ተግባር ባልጀመርንበት፣ ህዝባችን በርካታ ድጋፎች በሚፈልግበት ግዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ስለዚህም አሁን ያለንበት እና የገባንበት መድረክ በጥንቃቄ ከተያዘ፣ በአግባቡ ከተመራ ችግሮቻችንን ተሻግረን ወደ ምንፈልገው ቦታ ለመድረስ የሚያስችለን በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሻገር እንፈልጋለን ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ውሳኔ ጊዜውን ያልጠበቀ ከመሆኑም በላይ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም ዘላቂ ሰላምን፣ እፎይታንና ቅቡልነትን አያመጣም ሲል ተችቷል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 መሠረት ህ.ወ.ሓ.ት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ አለመፍታቱ እንደ ምክንያት አቅርቧል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የትግራይን የሽግግር መንግሥትን የፌደራሉ መንግሥት በበላይነት እንዲያቋቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም ሕወሓት በብቸኝነት የሽግግር መንግሥቱ አውራ ሲል ኮንኗል።

የህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር መሰረዝ የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እና ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት እንዳይሆን ስጋት እንዳለው የገለጸው ኢዜማ የፌደራል መንግሥቱ የስምምነት ግዴታዎቹን ሲወጣ ሕወሓትም ስምምነት ድንጋጌዎቹን ማክበሩን በጋራ በተቋቋመው ጥምር ኮሚቴ መረጋገጡን ከግምት እያስገባ መኾን እንደነበረበት አስታውቋል።

የሕወሓትን ቡድን ከሽብርተኝነት ሰርዞ ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት ነው ያለው ፓርቲው በህወሓት አማካኝነት ለሚደርስ ሀገራዊ ጉዳት ዋነኛ ተጠያቂዎች ገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት መሆናቸውን አመላክቷል። አሰ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.