ልዩ ዘገባ፡ በኢትዮጵያ ከለጋሾች የተገኘ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ የሚገኘው በተቀናጀ፣ በተደራጀ መንገድ መሆኑ ተገለጸ፤ ተግባሩ የፌደራል እና የክልል ተቋማትን ያሳተፈ በሰባት ክልሎች የተፈጸመ ነው ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1/2015 ዓ.ም፡- የአለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በትግራይ ክልል ተፈጸመ በተባለው ለተረጂዎች የቀረበ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ ውሏል በሚል ማቋረጣቸው ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት እና ለአዲስ ስታንዳርድ የደረሰው የውስጥ ማስታወሻ እንደሚያሳየው ከሆነ ድርጊቱ የተፈጸመው በትግራይ ብቻ አይደለም፤ ተግባሩ የፌደራል እና የክልል ተቋማትን ያሳተፈ በሰባት ክልሎች የተፈጸመ ነው። የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ላለፉት ሁለት ወራት ባካሄደው ሰፊ ክትትል እና ምርመራ በኢትዮጵያ በለጋሽ ድርጅቶች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ የሚገኘው በሀገር አቀፍ ደረጃ መሆኑን ማረጋገጡን የውስጥ ማስታወሻው አመላክቷል። ድርጊቱ በተቀናጀ መልኩ በተወሳሰበ የወንጀል መንገድ እንደሚፈጸም የጠቆመው ሰነዱ የምግብ እርዳታው ለተጎጂዎች እንዳይደርስ ድርጊቱ እንቅፋት መሆኑን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ እና መልሶ ማቋቋም ለጋሽ ድርጅቶች ቡድን በሰባት ክልሎች በሚገኙ 63 የዱቄት ፋብሪካዎች ላይ ያደረገው ክትትል እና ምርመራ የቀረቡ የምግብ እርዳታ እህሎች ላልታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጡን በውስጥ ማስታወሻው ተጠቅሷል።

ተግባሩ የተፈጸመው የፌደራል እና የክልል ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ መሁኑን የጠቆመው የምርመራ ውጤቱ ማስታወሻ የሀገሪቱ የመከላከያ ተቋም ክፍሎች ከሰብአዊ ረድኤቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አመላክቷል። በዱቄት እና እህል ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ተግባሩን በማመቻቸት ረገድ ሚና እንደነበራቸውም አስታውቋል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ባደረገው ክትትል ሌሎች ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች በሀገሪቱ ለሚገኙ ተጎጂዎች እንዲደርስ ያቀረቡት እርዳታ ላልታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጡን ጠቁሟል። ከፈረንሳይ፣ ጃፓን እና ዩክሬን የተገኙ በአለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት የቀረቡ እርዳታዎች ላልታለመለት አላማ መዋሉን ምርመራው ማረጋገጡን የውስጥ ማስታወሻው ላይ ተጠቅሷል።

እንደ ውስጥ ማስታወሻው ከሆነ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በመላ ሀገሪቱ የሚያካሂደውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ሊያቋርጥ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ያሳያል። የአሜሪካን መንግስት በ2022 ብቻ የአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ዶላር የህይወት አድን እርዳታ መለገሱ ይታወሳል።

ምንም እንኳ የተራድኦ ድርጅቱ የረድኤት ማቋረጥ ውሳኔ ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች ላይ ተጽእኖ ባይኖረውም ከዚህ በኋላ በአሜሪካ መንግስት እገዛ የሚካሄዱ ቀጣይ እርዳታዎች ከመከፋፈላቸው በፊት የሀገሪቱ የሰብአዊ ረድኤት ተደራሽነት አሰራር አስቸኳይ እና አስፈላጊ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተገልጿል።

በአጽንኦት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች

የኢትዮጵያ መንግስት እና የለጋሽ ማህበረሰቡ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ በሚል በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ እና መልሶ ማቋቋም ለጋሽ ድርጅቶች ቡድን ውይይት አስመልክቶ በቀረበው የውስጥ ማስታወሻ ላይ በዝርዝር ተቀምጧል። የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ባቀረበው ምክረ ሀሳብ ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች ይህን አጋጣሚ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ ረድኤት አቅርቦት አሰራር አደረጃጀትን ለማሻሻል እንዲጠቀሙበት አሳስቧል። የሰብአዊ እና መልሶ ማቋቋም ለጋሽ ድርጅቶች ቡድን በበኩሉ ባቀረበው ምክረሃሳብ የኢትዮጵያ መንግስት አስተማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ የጠየቀ ሲሆን ይህም መጀመር ያለበት የረድኤት አቅርቦቱ ላልታለመለት አላማ መዋሉን የሚኮንን ግልጽ መግለጫ በማውጣት መሆን አለበት ብሏል። በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የእርዳታ ሰራተኞች በምንም መልኩ ጫና እና እንግልት እንዳይደርስባቸው ሊጠብቃቸው ይገባል ሲል አሳስቧል። ለብልሹ አሰራር የሚዳርጉ ተቋማዊ አሰራሮችን በመለየት እንዲያስተካክልም ጠይቋል።

በስም ባልተጠቀሱ ክልሎች የተካሄደውን የምግብ እርዳታው ላልተገባ አላማ የዋለበትን መጠን አሳሳቢ መሆኑን ያመላከተው ቡድኑ የፌደራል መንግስቱ ከክልል እና ወረዳ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በህገወጥ መንገድ ተከማችተው የሚገኙ የእርዳታ አቅርቦቶችን በመለየት ሊያስመልሳቸው ይገባል ሲል በአጽንኦት ገልጿል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም ሃላፊዎች መልቀቅን የተመለከቱ እሰጣገባዎች

 

በኢትዮጵያ ከሰብአዊ ረድኤት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ውጥረት የነገሰ ይመስላል። በትግራይ ክልል የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ከሳምታት በፊት ማቋረጡን የገለጸው የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስራ ሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ዘኒው ሂዩማኒተርያን የተሰኘ ድረገጽ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ማስታወቁን የተመለከተ ዘገባ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት ተሰራጭቷል።

ዘኒው ሂዩማኒተርያን ድረገጽ ባስነበበው ዘገባ የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውዲ ጂቢዳር እና ምክትላቸው ጀኒፈር ቢቶንዲ የተቋሙ ሰራተኞች በተሰበሰቡበት መልቀቂያ ማስገባታቸውን በስብሰባ የታደሙ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።

የምርምራው ውጤት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ላይ ሃላፊው መልቀቃቸውን የጠቆመው ዘገባው የሃላፊዎቹ መልቀቅ ከተካሄደው የውስጥ ምርመራ ጋር ግንኙነት ይኑረው ወይንም አይኑረው ግልጽ አለመሆኑን አመላክቷል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ትዊተር ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ ጉዳዩን አስተባብሏል። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተቋሙ የኢትዮጵያ ሃላፊዎች ለቀቁ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ ነው ሲል ገልጿል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የተቋሙ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውዲ ጂቢዳር እረፍት ላይ መሆናቸውን እና አሁንም የድርጅታችን ባልደረባ ናቸስ ሲል ገልጿል። የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተሮች ሁሉም በስራ ላይ ይገኛሉ ሲል የገለጸው የአለም የምግብ ፕሮግራም ስራ መልቀቃቸው የተነገረው ምክትል ዳይሬክተሩ ጀኒፈር ቢቶንዲ ስራቸውን እያከናወኑ በተቋሙ ይገኛሉ ሲል ጠቁሟል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈልጉ ምንጭ እንደጠቆሙት ከሆነ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ እየጠየቃ ያለው ዋነኛ ነጥብ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ያሉ ሃላፊዎች እንዲቀየሩ ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉ አዲስ ስታንዳርድ የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ እና የፕሮግራሙ አለም አቀፍ የሚዲያ ተወካዮችን ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.