ዜና፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር መግባባት ላይ መድረሱን ገለፀ፤ የክልሉ መንግስት ትልቅና ዘመናዊ ቤተ እምነት መስሪያ ቦታ ይሰጣል ብሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1/2015 .ም፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም የተመራ ልዑክ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ከተመራ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ሀላፊዎች ጋር በሸገር ከተማ በፈረሱ መስጂዶች ዙሪያ ትላንት ግንቦት 30 ውይይት ተደርጎ የተደረሰበትን ምክር ቤቱ በዛሬው እለት መግለጫ አውጥቷል፡፡

በዚህም መሰረት በውይይቱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትበኩል ሕዝበ ሙስሊሙ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያየዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱንና ማዘኑን በማብራራት ተገቢውን ካሳና የሞራል ህክምና እንደሚያስፈልገው ተብራርቷል፤ እንዲሁም በሸገር ከተማ አስተዳደር ዉስጥ ያለ ፕላንና ሕጋዊነት ተሠርተዋል በሚል የፈረሱት 22 (ሃያ ሁለት) መስጊዶች መሆናቸውን በመጥቀስ ለሕዝበ ሙስሊሙ የመስጊጅ ጥያቄዎች በሙሉ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚገባ መጠየቁን መግለጫው አትቷል፡፡

በተጨማሪም ሸገር ከተማ አሰተዳደር ከፕላን ዉጭ ተሠርተዋል ያላቸውን መስጂዶች ለማፍረስ ሲነሳ የሚመለከተውን የእስልምና ጉዳዮች አካላትን እንዳላወያየ፣ እንዲሁም በጉዳዩላይ እንወያይ በሚል በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ለማወያየት አለመሞከሩ ተገቢ አለመሆኑ በቅሬታ መልክ ቀርቧል።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኩል ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ዉይይት አለመደረጉ ስህተት መሆኑን በመግለፅ የሸገር ከተማ የሃይማኖትን እሴትን መሠረት አድረጎ እንደሚገነባ እና የእሰልምናን ጨምሮ የሌሎችም ቤተእምነቶችም ተቋማት በብዛት በሸገር ከተማ ፕላን ዉስጥ ይካተታሉ ብሏል፡፡

አስፈላጊውን የቤተ-እምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥና በቆርቆሮ ሳይሆን የከተማዋን ፕላን የሚመጥን በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች በከተማው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉና በሸገር ከተማ ላይ በሀገር ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅና ዘመናዊ መስጂድና ለሌሎች እምነት ተቋማት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ገልጧል።

የክልሉ መንግስት ለኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚሆን መሬት እንደሚሰጥ በመግለፅ በሸገር ከተማ ሕግ ወጥ ግንባታን መከላከል፥ የተገነቡትን ማፍረስ እንደሚቀጥል ለዚህ ሂደት የእምነት ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ እንፈልጋለን በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ የሸገር ከተማ ፕላን ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ ሙሉ ለሙሉ መኖሪያ ቤቶች ባልፈረሱባቸው አከባቢዎች ለሚኖሩ ሙስሊሞች በጊዜያዊነት የሚሰግዱባቸው መስጊዶች የኦሮሚያ ክልል መጅሊስና የሸገር ከተማ አስተዳደር በጋራ በመጋገር መስጂድ መሥሪያ ቦታ እንዲያዘጋጁ ይሆናል ብሏል።

በሸገር ከተማ ሕዝበ ሙስሊሙ ያቀረባቸውና የሚያቀርባቸው የመስጂድ ጥያቄዎች በፕላኑ መሠረት ምላሽ እንደሚሰጥ እንዲሁም ሸገር ከተማን ጨምሮ በመላው ኦሮሚያ ክልል ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው የእምነት ተቋማት እና የመቃብር ሥፍራ መስጠት እንደሚቀጥል በፕሬድዳንቱ በኩል ተገልጧል።

ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ከጅምሩ በመነጋገር መፍታት እየተቻለ እስከ ትናንትናው እለት ድረስ መሰል ዉይይት ሳይደረግ መስጂዶችን ወደ ማፍረስ በመግባቱ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ቅሬታ ፈጥሮ ጉዳዩ እስከ ነፍስ መጥፋት ማምራቱ እጅግ አሳዞኖናል ያለው ምክር ቤቱ የጸጥታ አካላት ሰላማዊ ሙስሊሞች ላይ በቀጥታ በመተኮስ ሙስሊሞችን መግደላቸውና ማቁሰላቸው ተገቢ አለመሆኑን እንዲሁም ንጹሃን ላይ በመተኮስ የገደሉና ያቆሰሉ አካለት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።

የክልሉ መንግስት በሸገር ከተማ ዉስጥ ካሉት 800 የሁሉም እምነት ተቋማት መካከል 656 የሚሆኑት ከፕላን ዉጭ የተሠሩ በመሆናቸው እነዚህን የሚገነባውን ከተማ ፕላን የማይመጡትን የተለያዩ ቤተ-እምነቶችን ወደ በሕጋዊና ከተማውን በሚመጥኑ ተቋማት ለመተካት የሚደረገውን ሂደት የኦሮሚያ ክልል መጅሊስም ባለበት የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቅሙን በማጠናከር በዉይይት የእምነት ተቋማቱ ራሳቸው መፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈርሱ እንጂ ከአሁን በኋላ መንግስት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም ገልጧል። በተፈጠረው ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡት ሙስሊሞች ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.