ሸገር ዳቦ ለቀናት ስራ ማቆሙ ጫና እንደፈጠረባቸው ተጠቃሚዎች ተናገሩ

በማህሌት ፋሲል @MahletFasil

አዲስ አበና፤ የካቲት 11፤ 2014  በአዲስ አበባ ከተማ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች በድጎማ መልክ  የማያቋርጥ የዳቦ አቅርቦትን ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሸገር መጋገሪያ ከተመረቀ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ምርት በማቆሙወዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪወችን  ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል።

አዲስ ስታንዳርድን ያነጋገረቻቸው ሸማቾች እንደተናገሩት ሸገር መጋገሪያ ከዋጋ እና ከአቅርቦት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍም  ለህብረተሰቡ በተለይም  ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውን  ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። እንደሸማቾቹ ገለፃ የዳቦ አቅርቦቱ በመቋረጡ ምክያት በአሁኑ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል።

“መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ላለው የማህበረሰብ ክፍል ያቀረበዉ አንድ ነገር ይህ ብቻ ነበር እሱም ቆመ ተጎጂዉ ሙሉ በሙሉ  ይህ የማህበረሰብ ክፍል ነው ማለት ይቻላል’’

ወይዘሮ ዘነበች ቀለመወርቅ

ሁኔታው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረባት ወይዘሮ ዘነበች ቀለመወርቅ ገልጻለች። “ዋጋው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ለልጆቼ ዳቦ ልገዛ በጠዋት እነሳ ነበር። የአንዱ ዋጋ 1ብር ከ20 ሳንቲም ነበር የግል ዳቦ ቤቶች የሚሸጡት 3ብር ከ50 ሳንቲም እና ከዛ በላይ ነው። መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ላለው የማህበረሰብ ክፍል ያቀረበዉ አንድ ነገር ይህ ብቻ ነበር እሱም ቆመ ተጎጂዉ ሙሉ በሙሉ  ይህ የማህበረሰብ ክፍል ነው ማለት ይቻላል’’ በማለት  ለአዲስ ስታንዳርድ አብራርታለች።

አንዳርጋቸው ኑሮውን በቀን ስራ እየመራ ያለ ሲሆን በሁኔታው ተስፋ ከቆረጡ ተጠቃሚዎች አንዱ ነው። “ዳቦ ሁልግዜ ተሰልፌ አገዛለው ምሳዬን ይዤ ብሄድም በዳቦ ነው የምበላው ምክንያቱም አንድ እንጀራ 10 ብር ገብቷል በየቀኑ እንጀራ መግዛት አቅሜ አይፈቅድም ዳቦ ቤቶችም ሆኑ ሱቆች  ዳቦ በውድ ነው የሚሸጡት።  የሸገር ዳቦ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥቅም ነበረው መቆም የሌለበትን ነገር ነው ያቆሙት “ብሏል።

የኢትዮ-ሳዑዲ ቢሊየነር ሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ንብረት በሆነው በሚድሮክ ኢትዮጵያ  በ900 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይህ ዘመናዊ ዳቦ መጋገሪያ በሰኔ 2012 ምረቃ ላይ በተሰራጨ መግለጫ መሠረት በሰዓት 80,000፤  በቀን 1.8 ሚሊዮን ዳቦ ያመርታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

“ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ 10 ወራትን የፈጀው ሸገር ዳቦ መጋገሪያ የብልጽግና መንገዳችንን ማሳያ ነው።በሰአት 80,000 ዳቦዎችን  በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘቱ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ከተሞች ለምግብ ዋስትና ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፅንሰ-ሀሳቡን በማነሳሳት የወቅቱ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማን ጨምሮ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የዳቦ መጋገሪያውን ምረቃ ላይ ማድነቃቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ገና ከተመረቀ በስድስት ወራት ውስጥ  70 ሚሊዮን ብር ከዋጋ ንረት እና ከአቅርቦት እጥረት በተነሳ ችግር እንደከሰራ አሳውቆ ነበር። ይሁንና መጋገሪያው ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም የቆሙ የከተማ አውቶቡሶችን ጨምሮ በአዲስ አበባና አካባቢው በሚገኙ ከ400 በላይ የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችን በመጠቀም በቀን ከ700,000 እስከ 800,000 የሚደርሱ ዳቦዎችን በማምረት ምርቱን ለከተማው ነዋሪዎች ሲያከፋፍል ቆይቷል ።

በወቅቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመዲን ሸገር ዳቦ መጋገሪያ ለተጠቃሚዎች እየቀረበ ያለው ዋጋ  ከሚያስፈልገው ግበአት እንዲሁም ለስንዴ ግዥና ለአመራረት ሂደቱ ግብአት ጋር ሲነፃፃር ተመጣጣኝ አልነበረም ሲሉ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሸገር ዳቦ መጋገሪያና ዱቄት ፋብሪካ ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ  መስማማታቸው ተገልጾ ነበር። የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ ሃላፊ አዳም ኑር ለፋና ቢሲ የዳቦ መጋገሪያው አገልግሎት ማቋረጡን አምነው ቢሯቸው ከዋጋ ንረት ጋር የተነሳውን ጥያቄ እየመረመረ መሆኑን ተናግረዋል።   የከተማው አስተዳደር ለዳቦ መጋገሪያው በዓመት 309 ሚሊዮን ብር ድጎማ እየሰጠ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል። ሸገር ዳቦ ደግሞ 50 በመቶውን ወጪ ይሸፍን ነበር። ሸገር ዳቦ መጋገሪያ ወደ ስራው እንዲመለስ የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ነው።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮሙዩኒኬሽንና ማስታወቂያ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ተሾመ በበኩላቸው የግብአት እጥረት ዳቦ መጋገሪያው ምርቱን እንዲያቆም አስገድዶታል፤ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምርቱ በቅርቡ ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለተጨማሪ ማብራሪያ አዲስ ስታንዳርድ ሚድሮክ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.