ዜና፡ “በተቀበሩ ፈንጂዎች በርካታ ሰዎች እየሞቱና ጉዳት እየደረሰባቸው” በመሆኑ ፈንጂዎችን የማጽዳት እና የማስወገድ ስራ እንዲፋጠን ኢሰመኮ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ፣ 26/2015 ዓ.ም፡- በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተቀበሩና ጉዳት እያደረሱ ያሉ ፈንጂዎችን የማጽዳት እና የማስወገድ ተግባር ሊፋጠን እንደሚገባ እና መንግሥት ለፈንጂ ተጎጂዎች የማቋቋም እና የተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎችን ማቅረብ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት ሐምሌ 26፣ 2015 ባወጣው መግለጫ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከተከሰተው ጦርነት ተከትሎ ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በእርሻ፣ በውሃ መቅጃ እና በገበያ ቦታዎች እንዲሁም የትምህርት ወይም የጤና ተቋማትን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት መሠረታዊ ሕይወት ወደሚከወኑባቸው ሥፍራዎች በሚወስዱ መንገዶች አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል ብሏል፡፡

ለአብነትም በአፋር ክልል፣ ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት ምክንያት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው አልፏል ያለው ኮሚሽኑ፣ በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ደግሞ ወደ ዱብቲ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አስታውቋል፡፡ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን ኮሚሽኑ መረጋገጡን ገልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 23 ሕፃናት በፈንጂ ጉዳት እንደሞቱ፣ እንዲሁም ወደ 20 የሚገመቱ ተጨማሪ ሕፃናት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ከክልሉ አድዓር ወረዳ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል ብሏል፡፡

በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት በአዲአርቃይ ወረዳ ሥር ከሚገኙ 22 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ እና በደባርቅ ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሲኖሩ የቆዩ ተፈናቃዮች፣ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከመደረጉ በፊት አካባቢውን ወዳድቀው ከሚገኙ የጦር መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ የማጽዳት ሥራ ባለመከናወኑ ሕይወታቸው ያለፈ እና አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕፃናት መኖራቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል።

የኦታዋ ስምምነት አንቀጽ 6(3) የፈንጂ ተጎጂዎች (landmine victims) ተገቢውን የእንክብካቤ እና የተሐድሶ ድጋፍ ማግኘትን ጨምሮ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ተመልሶ የመካተት መብቶች እንዳላቸው መደንገጉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎችን የማጽዳት እና ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ተግባር እንዲፋጠን፣ ከማጽዳት ተግባሩ ጎን ለጎን መንግሥት ለፈንጂ ተጎጂዎች ሊደረጉ የሚገባቸውን የማቋቋም እና ተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎች እንዲያስፋፋ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅረቧል። 

ይህ በእንዲህ እያለ አዲስ ስታንዳርድ በሰኔ ወር በሰራው ዘገባ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት በተቀበሩ ተተኳሾች ሳቢያ አርሶ አደሮች የግብርና ስራቸውን ማከናወን እንዳይችሉ ማድረጉን ዘግቧል፡፡ በማዕከላዊ ትግራይ ቆላ ተምቤን የሚገኙ ገበሬዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት ያለ ምንም ስጋት ወደ ቀድሞ ህይወታቸው፣ ወደ ግብርናቸው መመለስ አልቻሉም፡፡

በቆላ ተምቤን ብቻ ሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና በርካታ እንሰሳት መሞታቸውን የወረዳው ባለስልጣን አቶ ገዛሀኝ አምቢዛ ገልፀዋል፡፡ በተቀበሩት ተንጂዎች ምክንያት ለተከታታይ ሶስት አመታት አርሶ አደሮች መሬታቸውን መረስ መቸገራቸውን የገለፁት ባለስልጣኑ ለክልሉ ግብርና ቢሮ ቢያሳውቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን በወቅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ አስ

 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.