እለታዊ ዜና፡ “በአማራ ክልል ያለው ግጭት እርስ በእርስ እያገዳደለና ሰብዓዊ ኪሳራ እያደረሰ” መሆኑን ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 26 / 2015 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በክልሉ “ያለው ግጭት እርስ በእርስ እያገዳደለና ሰብዓዊ ኪሳራ እያደረሰ” መሆኑን ገልፁ፤ ርእሰ መስተዳድሩ  “ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት ይምጣ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ጊዜያት ጀምሮ በክልሉ የፀጥታ ችግር አጋጥሟል ሲሉ ገልፀው መንገድ በመዝጋት የሰዎችን እንቅስቃሴ በመግታት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

እርስ በእርስ በመገዳደል ያመጣነው ለውጥ የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አሁን ያለው አካሄድ ክልሉን አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ ክልሉን ዋጋ የሚያስከፍል ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ ሁሉም ለሰላም መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።  

የክልሉ የፀጥታ መዋቅርና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ያስታወቁት ዶ.ር ይልቃል፣ የክልሉ ሕዝብ እየተከናወነ ያለውን ሕግ የማስከበር ሂደት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባል ነው ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ የኢትዮጵያውያን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ መከላከያን ያለ ስሙ ስም መስጠትና መተንኮስ አግባብ አይለምም ብለዋል።

ሁሉም ጥያቄ አለኝ የሚል ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መረባረብ አለበት በማለት የተናገሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል። የፀጥታ ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የክልሉ ሕዝብም ለሰላም በየአካባቢው ያለውን ትንኮሳ በማስቆም ሁሉም ወደ ሰላም እንዲመጣም ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገበው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።

በትላንትናው እለት ሓምሌ 25 የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሰጠው መግለጫ በ ፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ የሃገር ሰላም ለማወክ በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ሲል ገልጧል፡፡

የሰራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከሰሞኑ በጎንደር የሰሜን ምዕራብ እዝን ዓመታዊ አፈጻጸም ላይ ለመገምገም ወደ ስፍራው እያቀኑ በነበሩ የሰራዊቱ አባላት ላይ ከጩሂት 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርሱ ተኩስ በሰራዊቱ ላይ መከፈቱን በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

የሰራዊቱ አባላትም በመመለስ ላይ ሳለም በቆላድባ አካባቢ በተመሳሳይ ተኩስ ተከፍቷል በማለት አስታውቀው “ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ” የሚል አካል ላይ ሰራዊቱ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ሰራዊቱን መቋቋም ያልቻሉ አካላት በሰራዊቱ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.