ጥልቅ ትንታኔ:-ጎዶትን ጥበቃ: ወረርሺኝና ምርጫ በኢትዮጵያ

መሃሪ ታደለ ማሩ @DrMehari

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29, 2012 – የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርብ ጊዜ እንደገለፁት ገዢው ፓርቲ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ሥልጣን ይዞ ይቀጥላል፡፡ የኮቪድ-19ን መጨረሻና ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ መጠበቅ ግን ጎዶትን እንደመጠባበቅ ነው፤ ማንም መቼ እንደሚመጡ አያውቅም፡፡
ትርጉም ያለው ውይይት ከሕዝቡ ጋር ማድረግ በማይቻልባትና ጭካኔ የተሞላው ኃይል መጠቀም አዋጭ በማይሆንበት ሁኔታ ውስጥ ማጭበርበር፣ ሕግን በማስፈፀም ስም የሚደረጉ ግራ የሚያጋቡ ተግባራትና ብልሹ አሰራሮች የፖለቲካ ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ብቸኛዎቹ መሣሪያዎች ይሆናሉ፡፡ ግራምስኪ እንዳለው ‹‹ይህ ዓይነት ባህሪ የሚንፀባረቀው የበላይ ሥልጣን ይዞ መንቀሳቀስ አዳጋች ሲሆንና ኃይል መጠቀም ደግሞ አደገኛ በሚሆንበት ሁኔታ ወስጥ ነው››፡፡

የሒፖክራተስ ‹‹ጉዳት ያለማድረስ›› መሃላ
ነሐሴ 23, 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ ኮቪድ-19ን ምክንያት በማድረግ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙንየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 14, 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡ ምርጫ ቦርዱ እንደገለፀው ኮቪድ-19 በሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉት ላይ ‹‹ጉዳት›› ሳያደርስ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ይህን ጥሪ ሲያቀርቡ የሒፓክራተስን ‹‹ጉዳት ያለማድረስ›› መርህ መጥቀሳቸው ራሱ ይህን ምክንያት ያልተለመደና ግራ የሚያጋባ ያስመስለዋል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጨምሮ የዚህ ውሳኔ ደጋፊዎች ምርጫውን የሚያስተባብሩትንና በምርጫው ውስጥ የሚሳተፉትን ኢትዮጵያውያን ሕይወት ከጉዳት የመጠበቅ አስፈላጊነትን በሚመለከት ከምርጫ ቦርዱ ጋር እንደሚስማሙ ይገልፃሉ፡፡ ሌሎች ግን ኮሮናን ሰበብ በማድረግ ሥልጣን ለመያዝ የተደረገ ውሳኔ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን ያሰማሉ፡፡
የምርጫው መራዘም አስገራሚ አልነበረም፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ምርጫው እንዲራዘም የተለያዩ ወሬዎች ሲናፈሱ ከቆዮ በኋላ በተለምዶ በግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ከሦስት ወራት በኋላ ማለትም በነሐሴ እንደሚካሄድ በመወሰኑ የነበረው ውዠንብር እንዲጠራ ተደረገ፡፡ ይህ ውሳኔ ራሱ የምርጫ ሂደቱን ሊያስተጓጉል የሚችለውን በሰኔ ወር የሚጀምረውን የኢትዮጰያን የዝናብ ወቅት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግብርና አገር እንደመሆኗ ያለው የመጓጓዣ መሰረተ ልማት ለከባድ የአየር ንብረት የማይመችና ውሱንነው፡፡ ከዚህ ቀደም ምርጫን የማራዘም ልማድ እንዳለም መታወስ አለበት፡፡ በሚያዚያ4, 2010 ዓ.ም የፀጥታ ስጋት አለ በሚል ምክንያት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መካሄድ የነበረባቸው ምርጫዎች እንዲራዘሙ ተደርጓል፡፡

የሕገ መንግስቱ ማነቆ
የምርጫ ሂደት ባለብዙ ገፅታ ነው፡፡ የምርጫ አስፈላጊነት ማን ለምን ሥልጣን እንደሚይዝ ለመወሰን ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል ለመወሰን የሚረዳ ነው፡፡ ምርጫ መሰረታዊ መብቶችም ሥራ ላይ የሚውሉበት ሂደት ነው፡፡ ተወካዮችን በመምረጥ በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ እንዲሁም ማን የመመረጥ መብት እንዳለውና ማን መብቱ ሊኖረው እንደሚገባ የመወሰን ጉዳይ በሂደቱ ውስጥ የሚነፀባረቁት ዋና ዋናዎቹ መብቶች ነው፡፡ ምርጫ ከመሰረታዊ መብቶች ጋር ብቻ ሳይሆን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ጨምሮ ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም በፌደራላዊ ሥርዓት ውስጥ ካለው የሥልጣን ክፍፍል ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ባጠቃላይ እንዲሁም የክልል መንግስታት በተለይ በሽግግር ወቅቶች በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ፍላጎቶቻቸውን በተገቢው ደረጃ መግለፅ ተስኗቸው ለረዥም ጊዜ ቆይዋል፡፡ እነዚህ ወቅቶች ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበሩ በርካታ ብሔራዊ ጥቅምን፣ የሕዝብ ፖሊሲንና የሰዎችን ደህንነት የሚመለከቱ ፖሊሲዎች የሚለወጡባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡

በሕጉ መሰረት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ የአምስት አመቱ የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት መካሄድ አለበት፡፡ የፌደራሉ ሕገ መንግስት የነዚህ አካለት የሥራ ዘመን ሊራዘም የሚችልበትን አግባብ የሚመለከት ድንጋጌ አላካተተም፡፡ ስለዚህ መስከረም 30, 2013 ዓ.ም ላይ አዳዲስ የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች መሰየም ቢኖርባቸውም የሆነ ሕገ መንግስታዊ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር ሁለቱም ምክር ቤቶች አዳዲስ ተመራጮች አይኖሯቸውም፡፡ የፌደራል መንግስት ለዚህ አጣብቂኝ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ አራት ሕገ መንግስታዊ አማራጮች እንዳሉ ያምናል፡- የመጀመሪያው ፓርላማውን በመበተን ባላደራ መንግስት መመስረት፣ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሥራ ዘመኑን ማራዘም፣ ሦስተኛው ሕገ መንግስቱን ማሻሻል ወይም አራተኛው አማራጭ የሕገ መንግስት ትርጉም መስጠት ናቸው፡፡ አማራጮቹ ለአራት ተከፍለው ቢቀርቡም በተጨባጭ ግን የቀረቡት ሁለት አማራጮች ናቸው፡፡

ለነዚህ አማራጮች የተሰጡት ምላሾች ለሦስት ዋና ዋና አመለካከቶች ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው የሥራ ዘመኑን በማንኛውም መንገድ መራዘም የሚደገፍ ሲሆን ሕገ መንግስቱን ማሻሻል፣ የሕገ መንግስት ትርጉም ማፈላለግ ወይም እንደአስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይገልፃል፡፡የዚህ አመለካከት ደጋፊዎች አብዛኛዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሰት እየሰሩ ያሉና በጉዳዩ ላይ በድብቅ ስለሚደረጉ ውይይቶች እውቀት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በሁለቱም ምክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫ እንዳለው ስለሚታወቅ ይህን አመለካከት የሚያራምዱት ባለሙያዎች የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማደረግን ወይም ትርጉም መሰጠትን ይመርጣሉ፡፡ የነዚህ ቡድኖች አላማ ከሕግና ከወረርሺኝ ጋር የተገናኙ ክርክሮችን በማንሳት የመንግስትን ሥልጣን ማራዘም ነው፡፡ ይህ ቡድን ‹‹ቦታ የሚያሲዙ›› (‘the emplacement’) ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡

ሁለተኛው ቡድን የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ምርጫ መካሄድ አለበት የሚለው ቡድን ነው፡፡ እነዚህ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ሲቃረብ የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግን የሚቃወሙ ሲሆን ምክር ቤቱ የራሱን የሥራ ዘመን ለማራዘም የሚያደርገው ማንኛውም ሙከራ ግልፅ የሆነ የሕግ ጥሰት እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡የሕገ መንግስቱ ግልፅ የሆነ ድንጋጌን መተርጎም አስፈላጊ አለመኖኑን በአፅንዖት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም ከመስከረም 30 በፊት ምርጫ ካልተካሄደ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ኢሕገ መንግስታዊ ይሆናሉ በማለት ይከራከራሉ፡፡ ስለዚህ አንዳንዶቹ ምርጫው መካሄድ አለበት ሲሉ ሌሎች ደግሞ ምክር ቤቱን መበትን ብቸኛው ግልጽ የሆነው ሕገ መንግስታዊ አማራጭ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡እነዚህ ቡድኖች በሕገ መንግስት ላይ የተፃፈውን ብቻ መተርጎምን (textual interpretation of the Constitution)የሚደግፉ ሲሆን የሕገ መንግስት ትርጉም ሲሰጥ የመጀመሪያው/የቀደመው ሃሳብ ብልጫ እንዳለው የሚያምኑ (‘originalist’) በመሆናቸው ‹‹ሕገ መንግስታዊያን›› (‘constitutionalists’) ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ፡፡

ሦስተኛው ቡድን ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ትርጉም ያለው ውይይት በማድረግ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚፈልግ ነው፡፡ የዚህ ቡድን አብዛኛዎቹ አባላት አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት የማስወገድ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ምርጫው ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞ ብሔራዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት ይላሉ፡፡ እነዚህ ሽግግርን የሚያቀነቅኑ ሲሆን ‹‹ተተኪ›› (the ‘replacement’) በመባል ሊታወቁ ይችላሉ፡፡

የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ቡድኖች መንግስት ከምክር ቤት ውጪ ሊኖረው የሚችውን ቦታ ይቃወማሉ፡፡
በሕብረተሰቡ ላይ የተጋረጠው የጤና ስጋት፣ በፖለቲካው ያለው አነስተኛ ተቀባይነትና አጣብቂኝ መኖሩ ሊካድ የማይችል እውነታ ነው፤ ከዚህ ሁኔታ ሊያስወጣ የሚችል ቀላል መንገድ ደግሞ የለም፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ሕገ መንግስታዊ ተቺ የለም፡፡ ከባድ የሆነ ወረርሺኝ መከሰቱ፣ ከፋፋይ የሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መኖሩና ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ ኢትዮጵያን ታይቶ ወደማይታወቅ ሕገ መንግስታዊ ቀውስ ውስጥ ከቷታል፡፡

የወረርሺኙ ማብቂያ፡ ጎዶትን ጥበቃ
በሕብረተሰብ ጤና እና እንደ የመመርጥ መብት፣ የመንቀሳቀስ መብት፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና በምርጫ የመሳተፍን መብትን በመሳሰሉ መሰረታዊ መብቶች መካከል ሚዛናዊነትን ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ላሉ አከራካሪ በሆነ ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት ውስጥ በሚያልፉ አገራት ውስጥ ይህ ሥራ በቀላሉ ሊታይ አይገባም፡፡ ከሕብረተሰብ ጤና ጋር በተያያዘ በሚነሱ ችግሮች ምክንያት አንዳንድ መሰረታዊ መብቶች ሊጣሱ የሚችሉ ቢሆንም ጥሰቶቹ እንደአጭር ጊዜ እርምጃዎች ብቻ ሊታዩ ይገባል፡፡ ኮቪድ-19ን በሚመለከት የተለያዩ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተለያዩ ክልከላዎች ውጤታማነት በተለያዩ ከባቢያዊ ምክንያቶች ላይ ይመሰረታል፡፡በርካታ ወይም አብዛኛዎቹ የወረርሺኙ ገፅታዎች ላይ አሁንም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡ ነገር ግን የተረጋገጡ እውነታዎችም አሉ፡፡ ኮቪድ-19 በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ ነው፤ ስለዚህ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና እንቅስቃሴዎችን መገደብ መንግስታትም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለበሽታው ምላሽ የሚያዘጋጁበትን ጊዜ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ (አሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ ጥብቅ እርምጃዎች ቢወሰዱም ከሌሎች አገራት ክልከላዎች ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ ያለው ክልከላ ቀለል ያለ ነው፡፡) በእርግጥ በኮቪድ-19 የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ደረጃ ከጨመረ በሕዝብ ዘንድ ያለው የመንግስት ተቀባይነትና የአፈፃፀም ሕጋዊነት ፈተና ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡

ነገር ግን አሁንም ስለወረርሺኙ ብዙ የማይታወቁ ጉዳዮች እያሉ ምርጫን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማራዘም ያሉ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያመጡ ውሳኔዎችን መወሰን አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ የበሽታው ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስበትን ጊዜ እርግጠኛ ሆኖ መገመት ባይቻልም አንዳንድ ሞዴሎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር የሚመዘገው እ.አ.አ እስከ ግንቦት አጋማሽ 2020 ድረስ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ክትባት ለማግኘት ከአንድ አመት በላይ እንደሚወስድና የበሽታው የመስፋፋት ደረጃ በሰዎች መስተጋብር እንዲሁም አካላዊ ርቀትን እንዲጠበቅና ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ በሚወሰዱት እርምጃዎች እንደሚወሰን አብዛኛዎቹ ተመራማሪዎች ይስማማሉ፡፡ በእርግጥ በርካታ የእስያና የአፍሪካ አገራት አካላዊ ርቀትን መጠበቅንና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን መጠቀም የሚያስገድዱ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በድንበሮቻቸው ያለው ክልከላ ግን እንዲቀንስ አድርገዋል፡፡ ሆኖም በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርስበትን ጊዜና በሽታው ጨርሶ የሚጠፋበትን ጊዜ መገመት እንጂ በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም፡፡ የመንግስትን ሕጋዊነት የሚያረጋግጠውን ምርጫ ብሎም የአገርን ህልውና የማስቀጠልን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም ነገር በወረርሺኙ መጥፋት ላይ እንዲንጠለጠል ማድረግ ጎዶትን ከመጠባበቅ አይለይም፡፡ የአገሪቱን አስተዳደር እጣ ፈንታ ለመወሰን መጨረሻው የማይታወቅ ጉዳይን በመጠባበቅና በግምት የተነደፈ እቅድ አዋጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ስጋትን ሊቀንሱ የሚችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን በመወስድ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ከታሰበ ምርጫ ቦርዱ ‹‹ጉዳት ያለማድረስ›› መርህን እንደምክንያት በማስቀመጥ የወሰነው ውሳኔም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ እነዚህ አይነት እርምጃዎች በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ በትምህርት፣ በመገናኛ ብዙሃንና በጤና አገልግሎቶች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረጉ የአስፈላጊ አቅርቦቶች መጓደል እንዳይፈጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮቪድ-19 ቢኖርም ሕይወት ትቀጥላለች፡፡

የምርጫ ቦርዱ ሥልጣን የሚመነጨው ከፌደራል ሕገ መንግስቱ አንቀፅ 102 ነው፡፡ የምርጫ ቦርዱ ከመስከረም የመጨረሻው እሁድ 30 ቀናት በፊት ምርጫ የማካሄድ ሕገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት፡፡ ቦርዱ በምርጫው ውስጥ የሚሳተፉት ለአደጋ ሳይጋለጡ ምርጫ ማካሄድ አይቻለም የሚለው ውሳኔ ላይ እንዴት እንደደረሰ ግልፅ አይደለም፡፡ ይህ ውስኔ ከመወሰኑ በፊት የወረርሺኝና የጤና ባለሙያዎችን ለማማከር ተሞክሯል? ተሞከሮ ከነበረ ምን ዓይነት ሞዴሎችና ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ገብተው ነበር? ውሳኔውን ለመወሰን ከየትኞቹ ሞዴሎች የትኞቹ የጊዜ ገደቦች ተለይተው ወጡ?የምርጫ ቦርዱና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ ምን ያህል ጊዜ ለመጠበቅ ፍቃደኛ ናቸው? በሌሎች ሕብረተሰቡን በሚመለከቱ ዘርፎች ተግባራዊ የተደረጉት ስጋት የሚቀንሱ እርምጃዎች ለምርጫውም ጥቅም ላይ እንዲውሉ መጠየቅ የማይታሰብ ነው? ወረርሺኙ ለወራት ወይም ለአመታት ካልጠፋስ? የተዘጋጀው አማራጭ እቅድ ምንድነው? እነዚህ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ሳይሆኑ የምርጫ ቦርዱ ሊመልሳቸው የሚገባው እውነታዎችንና ሁኔታዎችን የሚመከቱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ወረርሺኙን በሚመለከት ስለሚሠራው ሥራና ስለሚያስከትለው ውጤት የተሻለ ግልፅነት ሊኖር ይገባል፡፡ መንግስት ድብቅ በሆነ መንገድ የተወሰኑ የሕግ ባለሙያዎችን ሰብስቦ የምርጫ ቦርዱ ያቀረባቸውን ሃሳቦች እንዲያዘጋጁ ማድረጉ የበለጠ ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል የተመረጠው አካሄድና የተፈጠረው ሕገ መንግስታዊ ማነቆ ለረዥም ጊዜ የቆየውን የአስተዳደር ተቋማትን ደካማነት የሚያጋልጥ ነው፡፡
በሕገ መንግስቱ መሰረት ‹‹ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል››፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 12 የመንግስት አሠራርና ተጠያቂነትን የሚመለከት ሲሆን የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ የግልፅነት መስፈርት ደግሞ የምርጫ ቦርድ ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ሲወስን የተካሄዱትን ጥናቶችና ከግምት ውስጥ ያስገባቸውን ጉዳዮችንም ያካትታል፡፡ ይህ መስፈርት አራቱን አማራጮች ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለፓርላማው ያቀረቡትንም አካላት ይመለከታል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሁኔታ
በሕገ መንግስቱ ላይ የተነሳው ክርክር ከወረርሺኙ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ኮቪድ-19 ያባባሰው በኢትዮጵያ ቀድሞ የነበረውን የመንግስትና የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡ አገሪቱ በተራጋጋ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፡፡ ዜጎች አሁንም አግባብ ያለሆነ ግድያ፣ እስራት፣ መፈናቀልና የኢኮኖሚ ውድቀት ሰለባ ናቸው፡፡ አሁን ግን ኮቪድ-19 ፖለቲካውን አልፎ ሁሉንም በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች አድርጓቸዋል፡፡
ይህን ምርጫ ልዩ የሚያደርጉት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ረዥም ጊዜ የፈጀ የሕዝብ አመፅ በወቅቱ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ እንዲለቁ ካስገደዳቸው በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር ቦታውን ተረክቧል፡፡ ገዢው ፓርቲ የነበሩት የፓለቲካ አቋሞችና አወቃቀሩ ተቀይረዋል፡፡ ምርጫው ቢካሄድ ኖሮ የሚካሄደው ገና ባልተጠናቀቀ የለውጥ ሂደት መሃል ነበር፡፡ ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሱ የተቀባይነት/የሕጋዊነት ችግሮች የወረርሺኙ ውጤቶች አይደሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ሳይነሳ የሚቀር ተቋም የለም፡፡ ወረርሺኙ የነበረውን የተበላሸውን አገራዊ ፖለቲካ ይበልጥ በክሎታል፤ የነፃና ፍትሃዊ ምርጫ መካሄድን ተስፋ አጨልሟል፤ በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የምርጫ ቦርድ ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከቷል፡፡ ቦርዱ አማራጮችንና የተለያዩ ስልቶችን ከመቀየስ ይልቅ ሥራውን ትቶ ቁጭ ብሎ ወረርሺኙን ለመመልከት የወሰነ ይመስላል፡፡ የምርጫውን እጣ ፈንታ ለመንግስትና ለሕዝብ ተወካዮ ምክር ቤት አሳልፎ ሰቷል፡፡

በኮሮና ሥልጣን መያዝ
እነዚህ ሁኔታዎች እያሉ አንዳንዶች ወረርሺኙን መንግስት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚጠቀመው አጋጣሚ እንደሆነ ይናገሩ ነበር፡፡ በሽታው ብዙ ስለተወራለት በብዙ ቦታዎች ‹‹በኮሮና ሰበብ ሥልጣን መያዝ›› የሚለው ሃሳብ ሊስፋፋ ችሏል፡፡ ይህ ጉዳይ እውነት ከሆነ በሌሎች አገራትም ስለታየ በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ ልዩ ነገር አይሆንም ነበር፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ አካላት የለውጥ ሂደቱ ቀላልና ፈጣን ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አመራር በከፍተኛ ልዩነት እንደሚያሸንፍ ጠብቀው ነበር፡፡ ሆኖም ጊዜው በሄደ ቁጥር የታየው የተቀባይነትና የአፈፃፀም ሕጋዊነት ማሽቆልቆል ለውጡ ከፊት ለፊቱ ከባድ ጎዳና እንደሚጠብቀውና የሚቀጥለው ምርጫ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አደጋች መሆኑ ግልጽ እየሆነ መቷል፡፡ ሥልጣን ለመያዝወረርሺኙ በረቀቀ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነም አንዳንዶች ይከራከራሉ፡፡

ሥልጣንን ተጠቅሞ ሕገ መንግስቱን መፃረር
የሕገ መንግስቱ አቋም ግልፅ ነው፡፡ አንቀጽ 54(1) እና አንቀጽ 58 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና[1] የአባላቱን[2] የሥራ ዘመን ወስነውታል፡፡ እነዚህ አንቀጾች ከአንቀጽ 8 እና ከአንቀጽ 9 ጋር በጋራ ሊነበቡ ይገባል፡፡ አንቀጾቹ ስለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት[3] እንዲሁም በሕገ መንግስቱ የበላይነት ሉዓላዊነታቸው በተመረጡት አካላት አማካኝነት የሚንጸባረቅ ስለመሆኑን የሚደነግጉ ናቸው፡፡ ከሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ውጪ መንግስትን መተካት ወይም ሥልጣን መያዝ ኢሕገ መንግስታዊ ነው፡፡[4] በተጨማሪም አሁን ያለው ክርክር በአንቀጽ 54 እና 58 ላይ ቢያተኩረም ከምርጫ ጋር በተያያዘ የመምረጥና የመመረጥ መብትን የሚመለከተውን አንቀጽ 38[5] ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡ መሰረታዊ የሆኑ የግለሰብና የቡድን መብቶችን የሚያካትተው አንቀጽ 38 ሲሆን በማናቸውም መልኩ ያለገደብ ሊጠበቁ የሚገባቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ያለውን መብት የሚሰጠው አንቀጽ 39 ቢሆንም ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ የማቅረብ መብት የተሰጠው ለሕግ አውጪ አካላት ነው፡፡ ምርጫን የሚያስፈፅመው አካል ደግሞ የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ሥልጣን ሥራ ላይ ማዋል ካልተቻለ በአንቀጽ 13 መሰረት የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች መከበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ ተቋማትና ዜጎችን ጨምሮ የሁሉም አካላት ግዴታ ይሆናል ማለት ነው፡፡[6]

በማሻሻያ ወይም በትርጉም ሥልጣን ማስያዝ
የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 104 የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብን ስለማመንጨት ሲሆን አንቀጽ 105 ደግሞ የማሻሻያ ሂደቱ የሚከተለውን ሥነ-ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶችን እንዲሁም አንቀጽ 104ን የሚመለከቱ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሁሉንም የክልል ምክር ቤቶች ድጋፍና በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የሁለቱን የፌደራል ምክር ቤቶች ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት አንቀጽ 39ን ጨምሮ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን መሻሻልና የሕገ መንግስቱን ማሻሻያ በሚመለከት የክልል ምክር ቤቶች የበላይ ሥልጣን አላቸው፡፡ የሥራ ዘመንን የሚመለከተው አንቀጽ 58ን ጨምሮ ሌሎች የሕገ መንግስቱን ድንጋጌዎች ለማሻሻል በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅና ከፌደሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤት ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምፅ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል፡፡ የተወካዮችን የሥራ ዘመን የሚመለከቱት አንቀጽ 58 እና አንቀጽ 54(1) የመምረጥና የመመረጥ መብትን ከሚደነግገው አንቀጽ 38 ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው፡፡ አንቀጽ 54 (1)ን በማሻሻል የፓርላማውን የሥራ ዘመን ማራዘም በየጊዜው መካሄድ ካለበት ምርጫ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ጋር የተያያዙትን መሠረታዊ መብቶች ዋጋ ያሳጣቸዋል፡፡
ማሻሻያ ማድረግና አላስፈላጊ ትርጉም ማሰጠት የሕገ መንግስት ተቋማቱን ደካማነትና ተቀባይነት ማጣት የበለጠ ያጋልጣል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ እንዳለው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስተር ኢንድራ ጋንዲ ሕንደን በሚመሩበት ወቅት ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረው ገዢ ፓርቲ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረጉን ማስታወስ ይቻለል፡፡ ይህ ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ የቆዩበት የሥራ ዘመንም አምባገነንነት የሰፈነበት ነው የሚል አመለከታከት በመስፋፋቱ በቀጣዩ ምርጫ ከመሸነፋቸው ባለፈ ወ/ሮ ጋንዲ ላይና የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ችግር ያለባቸው የሥነ-ሥርዓት አፈፃፀሞች ለሕገ መንግስታዊ ሥርዓቶች አደገኛ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በመጨረሻ ከሥነ-ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ የሕገ መንግስት ጉዳዮች የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ ድንጋጌዎች እንደመጣስ ስለማይታዩ ተፅዕኗቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሕገ መንግስቱ የሚጠይቀውን ሂደት አሟልቶ ተገቢውን የሥምምነት ደረጃ ማግኘት አለበት፡፡ ፍላጎት ያሳዩ አካላትን በመጋበዝመንግስት የሥራ ዘመኑን ለማራዘም የወሰነውን ውሳኔ የማሳመር ሥራ እንዲሰሩ መደረጉ ለሌሎች አክብሮት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም አደገኛ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሥራ ዘመን ለማራዘም ሕገ መንግስት ማሻሻል በበርካታ የሰብ ሰሃራ አገራት የታየ ሲሆን ለሕግም ሆነ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ የማይሰጥ ከመሆኑ በተጨመሪ አደገኛ ተምሳሌት መፍጠሩ አይቀርም፡፡

በተመሳሳይ የሕገ መንግስት ትርጉም በማያስፈልግበት ሁኔታ ትርጉም እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረብ አደገኛ ነው፡፡ ውስብስ የሆነውን የፖለቲካ ማትሪክስ ሥልጣን ፍለጋ ላይ ያተኮረ ‹‹የቁጥር ፖለቲካ›› ያደርገዋል፡፡
የሕገ መንግስት አጣሪ የሚያስፈልገው ሕገ መንግስትዊ ክርክሮችን ሊያስነሱ የሚችሉ ክፍተቶች ሲያጋጥሙ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሕግ ወይም ውሳኔ የሕገ መንግስቱን መርህ ወይም ድንጋጌ ይጥሳል የሚል ሰው ቅሬታ ሲያቀርብ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ግልፅ ያልሆኑ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን መተርጎም ተቀባይነት የሚያገኘው ሕገ መንግስታዊ ክርክሮች ከተፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ የፌደራል ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 83 እና አንቀጽ 84 ግልፅ ናቸው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ‹‹የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርብለት ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ›› ላይ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ሲኖረው ጉባዔው ‹‹በፌደራሉ መንግስትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከዚህ ሕገ መንግስት ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳና ጉዳዩን በሚመለከተው ፍርድ ቤት ወይም በባለጉዳዩ ሲቀርብልት›› ‹‹ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን›› አለው፡፡ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሥራ እንዲጀምር ሕገ መንግስታዊ ክርክር መነሳት እንዳለበት ከነዚህ ድንጋጌዎች ማየት ይቻላል፡፡ የአጣሪ ጉባዔውን የሚመለከተው አዋጅም ተመሳሳይ መርሆችን ይደነግጋል፡፡

ሕገ መንግስቱን ወይም ይዘቱን በሚመለከት የተለያዩ አማራጮች ወይም አስተያየቶችመቅረባቸው ክርክር መኖሩን አያረጋግጥም፡፡ አይደለም አማራጮችን በፍርድ ቤት ክርክር የተነሱ በርካታ ጉዳዮችን የሕገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ጉባዔው ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡
በሌሎች አገራት ይህን መሰል አካላት ምክረ ሃሳብ ወይም የውሳኔ ሃሳብ የመስጠት ሥልጣን የሚሰጣቸው ልዩ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የፌደራሉ ሕገ መንግስት የዚህ ዓይነት ምክረ ሃሳብ የመስጠት ሥልጣን ለጉባዔው አይሰጠውም፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤቱና አጣሪ ጉባዔው በዚህ መልክ ምክር የሚሰጡ አካለት ሆነው አያውቁም፡፡ እንዳውም በቅርብ ጊዜ ከቤተሰብ ሕግ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ጉባዔው ሊነሱ በሚችሉ ሕገ መንግስታዊ ክርክሮች ላይ ምክረ ሃሳብ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህ ምክንያት ሁለቱም አካላት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበላቸውን የምክረ ሃሳብ ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡

የምክረ ሃሳብ ወይም የውሳኔ ሃሳብ የማፈላለግ አማራጭ ከፀደቀ የፌደሬሽን ምክር ቤቱና አጣሪ ጉባዔው አማካሪ አካላት ስለሚሆኑ ደረጃቸው ዝቅ ይላል፡፡ በፌደራልና በክልል ያሉ ሕግ አውጪ አካላት በሚሰበሰቡበት ወቅት የሚነሱ ፖለቲካዊ ክርክሮችን የሕገ መንግስት ትርጉም ጉዳይ እያደረጉ ለአጣሪ ጉባዔው የትርጉም ጥያቄ እንዲያቀርቡ ከተፈቀደላቸው ጉባዔው በጥያቄዎች መጨናነቁ አይቀርም፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫውን ለማራዘም ወስኗል፡፡ ይህ በተግባር ሕገ መንግስቱን እንደማሻሻል ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል ይኸው ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጠው ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ የቀረበው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከነበረ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊት የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄ የሚሰጠውን ምላሽ መጠበቅ ነበረበት፡፡ ፓርላማው ምርጫውን ለማስተላለፍ ወስኖ እያለ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ አቅራቢም መሆን አይችልም፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላ በውሳኔው ቅር የተሰኘ አካል ቅሬታውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርብ ኖሮ ሂደቱ በትክክለኛ መንገድ ይጓዝ ነበር፡፡ አሁን የተደረገው ከመስከረም በኋላ መንግስት ሥልጣኑን ይዞ ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም በሚለው ጉዳይ ላይ ፓርላማው ራሱ ውሳኔ ሳይሰጥ የምክረ ሃሳብ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ጥያቄ እንዲያቀርብ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መሰረታዊ የሆኑ የፍትህ መርሆችን የሚያቃልል ነው፡፡ በሌላ በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና የሆነውን ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌደሬሽን ምክር ቤቱ የሚያስተላለፍ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ተግባር የሥልጣን ዘመኑ መራዘሙ ተቀባይነት ያገኛል በሚል ተስፋ የአንዱን ኃላፊነት ወደሌላ የማስተላለፍ እንቅስቃሴ ነው፡፡
በመጨረሻ የፌደራል ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60 ላይ የተፃፈውን እንዳለ በማንበብ አሁን ላለው ክርክር መፍትሄ ማግኘት ይችላል፡፡ ትርጉም የሚፈልግ የሕገ መንግስት ክፍተት ወይም ክርክር (ቢያንስ እስካሁን) የለም፡፡ እስካሁን ባስተናገዳቸው አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ውስጥ አጣሪ ጉባዔው እንደፍርድ ቤት በመሆን የሕገ መንግስት ትርጉም የሚፈልጉ ክርክሮችን ብቻ ሲዳኝ ቆይቷል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶች ላይ ገደብ ያስቀምጣል እንጂ በሕገ መንግስት የተወሰነውን የሥራ ዘመን ሊያራዝም አይችልም፡፡ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይዘትና አዋጁ ስለሚታወጅበት ሥነ-ሥርዓት የሚደነግገው አንቀጽ 93 ይህን በግልፅ ያስረዳል፡፡[7] በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ያስከተለውን ጉዳይ ለማስቀረት እስከሚያስችለው ደረጃ ድረስ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉትን የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶች መገደብ ይችላል፡፡ ሰባቱ የሕጋዊነት መርሆች (አዋጅ፣ ተመጣጣኝነት፣ የማይሻሩ መብቶች መኖር፣ የጊዜ ገደብ፣ ልዩ ሥጋትና መድልዎ አልባነት) ተፈፃሚነጽነት አላቸው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያግዳቸው ወይም ሊገድባቸው የማችላቸው አንዳንድ መሰረታዊ የማይሻሩ መብቶች አሉ፡፡ እነዚህም ስለአገሪቱ ስያሜ የሚመለከተው አንቀጽ 1 (ማለትም ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ)፣ አንቀጽ 18 (ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ) እና ስለእኩልነት መብት የሚደነግገው አንቀጽ 25 ሊታገዱ ወይም ሊገደቡ አይችሉም፡፡ ሕገ መንግስቱ ለብሔሮች የሰጠውን ልዩ ትኩረት በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ አንቀጽ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን መብት በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የመንከባከብ መብታቸውን የሚያረጋግጥ ሲሆን መብቶቹ በማናቸውም መልኩ ሊገደቡ ወይም ሊታገዱ አይችልም፡፡

ከላይ የተገለፁትን አብዛኛዎቹን መርሆች የሚፃረር ስለሚሆን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሥራ ዘመን ለማራዘም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መጠቀም እንደማይቻል ከሕገ መንግስቱ መግቢያ መረዳት ይቻላል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሥልጣን ጊዜን ማራዘም መሰረታዊ የሆኑትን የመምረጥና የመመረጥ መብቶች ከማቃለሉ ባለፈ በበርካታ የአፍሪካና የደቡብ አሜራካ አገራት የታየውን ያላግባብ የአስቸኳይ ጊዜን የማራዘም አዝማሚያ መድገም ይሆናል፡፡በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜው በተራዘመ ቁጥር በአንቀጽ 30 ላይ የተደነገጉት የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብቶች እንዲሁም በአንቀጽ 31 የተደነገገው የመደራጀት መብት በከፍተኛ ደረጃ መዳከማቸው አይቀርም፡፡

በአጠቃላይ ወረርሺኙን ምክንያት በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንደማወጅ ያሉ ጠንካራ እርምጃዎች ‹‹በሽብር ላይ እንደታወጀው ጦርነት›› አይነት መሳሪያዎች ሲሆኑ ወረርሺኙ ወይም ሽብሩ ካላፈ በኋላም የመቀጠል አዝማሚያ አላቸው፡፡ ‹‹በሽብር ላይ የታወጀው ጦርነት›› ሽብሩ ከሚገድላቸው ሰዎች በላይ ሊገድል እንደሚችል ሁሉ በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከቫይረሱ በላይ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች እንደማደንዘዣ ወይም እንደማስተገሻ ናቸው፡፡ በሽታውን ሊፈውስ ከሚችል መድሃኒት ጋር አብረው ካልተወሰዱ በጊዜ ሂደት ከበሽታው በላይ ገዳይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወረርሺኙ የተወሰኑ ሰዎችን ሊገድል ይችላል፤ አምባገነናዊ አስተዳደር ግን አገሪቱን ሊገድል ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጠቀም የመንግስትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀየሰው ዘዴ በግልፅ፣ በአጽንዖትና በፍጥነት ተቀባይነቱን ማሳጣት ያስፈልጋል፡፡

ባላደራ መንግስት፡ ሕገ መንግስታዊው አማራጭ
የፓላማውን የሥራ ዘመን የሚመለከተው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 58 እና ስለመምረጥና መመረጥ መብት የሚደነግገው አንቀጽ 38 ስለፓርላማው መበተን ከሚደነግገው አንቀጽ 60 ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው፡፡ ፓርላማው ከተበተነ በኋላ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ባላደራ መንግስት ይሆናል፡፡ ሥሙ እንደሚያመላክተው የዚህ መንግስት ዋና ዋና ኃላፊነቶች ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በጊዜያዊነት ሥልጣኑን በመያዝ የዕለተ ተዕለት የመንግስትን ተግባራት ማከናወንና ቀጣዩን ምርጫ ማስተባበር ናቸው፡፡ ጊዜያዊ ባላደራ መንግስት እንደመሆኑ አዳዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም፡፡

ምንም እንኳን ሕገ መንግስቱ የባላደራ መንግስት ጉዳይን በማያሻማና ግልጽ በሆነ መልኩ ቢያካትትም ከቀረቡት አማራጮች ሁሉ አነስተኛውን ትኩረት የሳበ አማራጭ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ኮቪድ-19ን ለመዋጋት ጠንካራ አመራር ስለሚያስፈልግ የዚህ ዓይነት መንግስት መመስረቱን እንደማይቀበሉ ገልፀዋል፡፡ ይህ ክርክር ግን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ክርክሩ አሁን ያለው መንግስት ጠንካራና የተረጋጋ እንደሆነ ታሳቢ ያደርጋል፡፡ሁለተኛ ወረርሽኝን ለመዋጋት ተግባራዊ የሚደረገውን መፍትሄ ሊመራ የሚችለው ብቸኛው አካል የፌደራል መንግስት እንደሆነ ታሳቢ ያደረግል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጰያ ታሪክ ውስጥ ከዚህ በላይ ደካማ መንግስት የታየበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው፡፡ በርካታ ምሁራን አሁን ያለውን ሁኔታ ከዘመነ መሳፍትንት ጋር ያነፃፅሩታል፡፡ አገሪቱ በተግባር በኮንፌደሬሽን ሥርዓት ውስጥ ሆና አብዛኛዎቹ ክልሎች ደግሞ በመከላከያ ሠራዊቱ ቀጥተኛ አስተዳደር ስር መሆናቸው ከባድና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለን ያሳያል፡፡ አሁን ውጤታማ በሆነ ደረጃ ኮቪድ-19ን እየተዋጋ ያለው ማነው ብሎ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፤ የፌደራል መንግስት ወይስ የክልል መንግስታት? በሌላ በኩል ለውጥ እያመጡ ያሉት የመንግስት አካላት ናቸው ወይስ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት? የአንድ መንግስት ጥንካሬ የሚመነጨው ከተቀባይነቱ ሲሆን ይህን ተቀባይነት የሚያገኘውም ውጤታማ የሆነ አፈፃፀም በማስመዝገብ እና/ወይም ሕዝባዊ ተቀባይነትን ለማግኘት ከሚከተላቸው ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችን ነው፡፡ አሁን ያለው መንግስት ሁለቱም ባሕሪያት የሉትም፡፡ በተፈጠረው ማህበራዊ አለመረጋጋት ምክንያት በርካታ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ቆመዋል፡፡ እየታየ ያለው ሕገ መንግስታዊ ቀውስ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ግድ የለሽ የዴሞክራሲ ሁኔታ በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡ ኮቪድ-19 ምንም ይሁን ምን ቀጣዩ ምርጫ ካልተጭበረበረ በስተቀር አሸናፊ ሆነው የሚወጡት ሥር የሰደደና ጠንካራ ማህበረሰባዊ ድጋፍ እንዲሁም ግልፅ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ናቸው፡፡

ሕግና ፖለቲካ ላይ መቆም
ሕገ መንግስት በሕግና በፖለቲካ ላይ ሊቆም ይገባል፡፡ ሕገ መንግስት የሕግ ሰነድ ሲሆን ሕዝባዊ የፖለቲካ መድረኮች ጋር መድረሱ አስፈላጊና የሚበረታታ በመሆኑ በሕግ ባለሙያዎች እጅ ብቻ ሊተው አይገባም፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየታየ ያለው የጦፈ ክርክር አንድ ቁም ነገረን ያመላክታል፡፡ ምንም እንኳን እየቀረቡ ያሉት ሙያዌ የሕገ መንግስት አማራጮች ቢመስሉም እየተካሄደ ያለው ክርክር የሕግ ጥያቄን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ጉዳዩ ፖለቲካዊም ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሄውም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው የደህንነት ሥጋት በበዛበት፣ ጥያቄ ውስጥ የገባ ተቀባይነት ባለበትና መንግስት ፖሊሲዎቹን የራሱ አድርጎ ማስቀጠል የሚችልበት አቅሙ ላይ ጥያቄ በተፈጠረበት አደገኛ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ ነው፡፡

ነሐሴ ውስጥ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ ከተራዘመ፣ ፓርላማውም ካልተበተነና ባላደራ መንግስት ካልተቋቋመ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በግልጽ የፌደራል ሕገ መንግስቱን አንቀጽ 54(1) እና 58(3) ይጥሳል ማለት ነው፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ሥርዓት ገንቢ የሆነ የውይይት ሂደት ላይ እንደማይደርስ ወይም መድረስ እንደማይችል የሚያሳይ ይሆናል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ቦታውን ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ (Emplacement) ኢሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን ላይ የመቆየት ያህል ሕገ መንግሰቱን መጣስ ይሆናል፡፡
በፍጥነት ስምምነተ ላይ መድረስ ካልተቻለ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የሥራ ዘመን እንዲሁ መራዘሙ አይቀርም፡፡ በጊዜ ሂደት ደግሞ አምባገነናዊ የመንግሰት አስተዳደር ሥርዓት የመመለሱ እድል ሰፊ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉ ሰፋፊ ሕዝባዊ አመፆች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡

ሊተገበር የሚችል መፍትሄ፡ አሳታፊ የሆነ ባላደራ መንግስት
አጥጋቢ የሆነ ሕገ መንግስታዊ መፍትሄ በሌለበት ሁኔታ ብዙም አጥጋቢ ያልሆኑት አማራጮች ከግምት ውስጥ ሊገቡ ይገባል፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ምርጫውን በጊዜው ማካሄድ ነው፡፡ ይህ ግን በወረርሺኙ የመስፋፋት ደረጃና ጉዳቱን ለመቀነስ ሊወሰዱ በሚችሉ እርምጃዎች ይወሰናል፡፡ ሁሉተኛው አማራጭ ባላደራ መንግስት በማቋቋም የተፈጠረውን ሕገ መንግስታዊ ማነቆ ለመፍታት የሚያስችልና ሊተገበር የሚችል ፖለቲካዊ መፍትሄ ማፈላለግ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱ የዚህ ዓይነት መንግስት እንዲቋቋም የሚፈቅደው አሁን እያስተዳደረ ያለው አካል ከተበተነ በኋላ መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም፡፡[8]
ባላደራ መንግስት የሚወስናቸው ውሳኔዎች የዕለት ተዕለት የመንግስት ሥራዎችን ከማከናወን ጋር የተያያዙ ብቻ ናቸው፡፡ ስለሆነም በሚቀጥለው ምርጫ የሚመረጠው መንግስት ላይ መስተጓጎል ሊፈጥሩ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማስተላለፍ ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተውና ተስማምተው ከሚፈቅዱለት በላይ ከፍተኛ ሃብት ወጪ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረብ አይችልም፡፡ የባላደራ መንግስት ዋናው አላማ ምርጫውን በተቻለ ፍትጥነት በማካሄድ ለተመረጠው መንግስት ሥልጣን ማስተላለፍ ነው፡፡

‹‹አሳታፊነት›› በሂደቱ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሴቶች ጉዳይና ተሳትፎን ጨምሮ የተለያዩ አመለካከቶችና አቋሞች ስላሉ ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን በማካሄድ እንዲሁም በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖር በማድረግ አሳታፊነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሳታፊ መንግስት ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በተቻለ መጠን በአጭርና በተገደበ ጊዜ ውስጥ ሥራውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ሐቀኝነትን ጨምሮ ገንቢ በሆነ መልኩ አብሮ ለመስራት እንዲሁም ገዢው ፓርቲ፣ ተቃዋሚዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተስማምተው የወሰኑትን ውሳኔ ለማስፈፀም ተነሳሽነትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡

መራጩ ማህበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ በተከፋፈለበት በአሁኑ ወቅት ባላደራ መንግስት ለአገሪቱ በርካታ ጠቀሜታዎችን ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ይህ ባላደራ መንግስት በአሳታፊነትና በውይይት ላይ የተመሰረተ ሂደትን ከተከተለና በሚቀጥለው ምርጫ የማይወዳደሩ የተመረጡ ገለልተኛ የምክር ቤት አባላት ከተሳተፉበት በታማኝ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ፉክክር ያለበት ምርጫ ለሚመረጠው መንግስት አስተማማኝ ድልድይ በመሆን ለኢትዮጵያ የአዲስ ጅማሬ እድል ሊሰጥ ይቸላል፡፡ ግልጽነትን ለማረጋገጥ በየጊዜው እየተሰራ ስላለው ሥራ ማብራሪያ በመስጠት፣ የሚድያ መግለጫዎችን በማዘጋጀት፣ እንደአስፈላጊነቱ ቃለ መጠይቆችን በማካሄድና መረጃ የሚራጭበትን አካሄድ ለመወሰን ፕሮቶኮሎች በማዘጋጀት ግልጽነትን ማረጋገጥ ይችላል፤ ማረጋገጥም አለበት፡፡ ይህን በማድረግ በቀጣይ ሊገጥመን ለሚችለው ፉክክር የተሞላበት የጥምረቶች ፖለቲካ ኢትዮጵያን ማዘጋጀት ይችላል፡፡ ባላደራ መንግስት ማቋቋም ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረገው ሽግግር አመኔታ የሚገነባ እርምጃም ሊሆን ይችላል፡፡
ከሁሉም በላይ አሳታፊ የሆነ ባላደራ መንግስት መመስረት ሰላምና መረጋጋትን ሊያረጋግጥ የሚችል ተጨባጭ ለውጥ ለኢትዮጵያ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የመንግስት ባህሪ ምን መምሰል እንዳለበትና ከሕዝቡ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው ይገባል በሚለው ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻል ኢትዮጵያ በታሪኳ በተደጋጋሚ ሲገጥማት የኖረ ችግር ነው፡፡ በቀጣይ የሰከነ ሕሊና እንዲገዛ ከተፈለገ ይህ አማራጭ ዘመን ተሻጋሪ ለሆነው ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ታሪካዊ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡
የኤዲተር ማስታወሻ፡ ዶ/ር መሃሪ ታደለ ማሩ በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲ ተቋም የትርፍ ጊዜፕሮፌሰር (መምህር) ሲሆኑ በሚቀጥለው አድራሻ ሊገኙ ይችላሉ፡mehari.maru@eui.eu

[1]የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት አመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡ የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት እስከ ሰኔ 30 ነው፡፡
[2]የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡
[3]የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህ ሕገ መንግስት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነተ ይሆናል፡፡
[4]ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠረር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግስቱን የማስከበርና ለሕገ መንግስቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ሕገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡
[5]ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚከተሉት መብቶች አሉት፡- በቀጥታና በነፃነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይአስተዳደር የመሳተፍ፤ በሕግ መሰረት የመምረጥ፤ በማናቸውም የመንግስት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ፡፡
[6]በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግስትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሰረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሠነዶ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ፡፡
[7]የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌደራል መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
[8]ምንም እንኳ አወዛጋቢ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነት ሥነ-ሥርዓትን ተግባራዊ የማድረግ ልምድ አላት፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላየፌደራሉ መንግስት በአምባሳደር ብርሃኑ ደሬሳ የሚመራ ሙያዊ የከተማ አስተዳዳር ባላደራ መንግስት በአዲስ አበባ እንዲቋቋም አድርጎ ነበር፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.