ዜና፡ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የአማራ ክልል ዋና ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ከተሞቹ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ መጀመራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ባህርዳር ከተማ – (ፋይል )  ፎቶ – ከባር ዳር ከተማ ኮሙኒኬሽን ፌስቡክ ገፅ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5/2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ገደቦችን ማስቀመጡን እና የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ወደ ስራ እንዲገቡ ማዘዙን ተከትሎ በክልሉ የግጭት ቀጠና የሆኑ ዋና ከተሞች ወደ መረጋጋትና መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ መጀመራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ  የባህርዳር ነዋሪ መከላከያ ሰራዊት ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯል ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል፡፡ ነዋሪው “ በከተማዋ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ የመመለስ አዝማሚያ ቢኖርም  የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ግን በዋናነት በመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች ብቻ የተገደበ ነው” ብሏል። ከዚ ውጭ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ ዋና መንገዶች ከተፀዱ በኋላ በእግርና በሳይክል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡

ሌላኛው በባህር ዳር የድሮ ዲፖ በሚባል አከባቢ ነዋሪ የሆነችው  ምንጫችን አዎንታዊ ለውጦች መኖራቸውን ለአዲስ ስታንዳድ ገልፃለች፡፡ “ የኤልክትሪክ አገልግሎት መመለሱንና ሆስታሎች በሙሉ አቅም አገልግሎች እየሰጡ” ነው ስትል ገልፃ ነገር ግን የባንክ አገልግሎት በማስጀመር ረገድ የተወሰቡ ክፍተቶች መሆራቸው ተናግራለች፡፡

በሻዋሮቢት ከተማ እንቴርኩ አካባ ነዋሪ በከተማው ውስጥ እንቅስቃሴ መኖሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል ። ተሸከርካሪዎች በከተማዋ ውስጥና ወደ አዲስ አበባ እየተንቀሳቀሱ ነው ያለው ነዋሪው ከሌሎች አገልግሎቶች በተለየ ባንኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ አይደሉም ብሏል፡፡  

ሮይተርስ የዜና ወኪል ረቡ ባወጣው ዘገባ የመንግስት ሃይሎች ጎንደር እና ቅዱሷን ከተማ ላሊበላን መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡

ማክሰኞ እለት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላን ከታጣቂ ሃይሎች ነጻ ማውጣቱን ገልፆ በከተሞቹ የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ክፍት እንዲሆኑ አዟል፡፡ በተጨማሪም በከተሞቹ ክልከላዎችና ገደቦችን አስቀምጧል፡፡

ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች እና የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ግጭቱ በርካታ ንፁሃንን ህይወት ቀጥፏል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ ግጭቱ አብዛኛው ህዝብ ተሰባስቦ በሚኖርባቸው ከተሞች መካሄዱን፤ የንጹኃንን ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ፤ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች መገደቡን፤ የክልሉን ሰላም በእጅጉ ማወኩን፤ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለው ብሏል፡፡ ምክር ቤቱ በግጭቱ ተዋናይ ቡድኖች ለዘላቂ ሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ (ICHREE) በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ እጅጉን እንዳሳሰበው ገልፆ መንግስት በክልሉ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያስፈጽምበት ወቅት የአስፈላጊነት መርሆችን እንዲከተል ፣ የተመጣጠነ እንዲሆን እና አድሎአዊ ያልሆነ አሰራርን በጥብቅ እንዲከተል አሳስቧል

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ሁለቱም አካላት ሰብዓዊ መብቶጭን እንዲያከብሩና ሁኔታውን ለማርገብ እና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቅድሚያ እንዲሰጡ” ጥሪ አቅርቧል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.