አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/ 2015 ዓ.ም፡– ኢትዮ ሰላም የተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል መስራች ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ቴዎድሮስ አስፋው እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ጋዜጠኛ ዲያቆን ዮሴፍ ከተማመታሰራቸው ተገለጸ።
ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ቴዎድሮስ ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ኃይሎች ተወስዶ መታሰሩን ወንድሙ ቢንያም አስፋው በቻናሉ ቀርቦ በሰጠው ቃለምልልስ አስታውቋል።
ትላንት የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምንት ሰዓት አከባቢ ሁለት የታጠቁ እና አራት ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ሀይሎች ከቤቱ እንደወሰዱት የተናገረው ወንድሙ የተሰጠው ምክንያት ለጥያቄ ትፈለጋለህ የሚል ብቻ እንደነበር አመላክቷል። ምንም አይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዛቸውንም ጠቁሟል።
በእስር ያለበት ቦታ እንደሚታወቅ የተናገረው ቢኒያም በአሁኑ ወቅት ሜክሲኮ አከባቢ በሚገኘው የፌደራል ወንጀል ምርመራ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ስለ ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረቡ ጉዳይ የሚታወቅ ነገር የለም ብሏል።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው በወቅታዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የከረረ ትችት በመንግስት ላይ በማቅረብ ይታወቃል። ቴዎድሮስ ለመጨረሻ ግዜ በዩቱዩብ ቻናሉ ያቀረበው ዝግጅት ከአምስት ቀናት በፊት ‘’ከሲኖዶሱ ህልውና ጋር የተያያዘው ሰላማዊ ሰልፍ’’ በሚል ርዕስ እንደነበር ከቻናሉ ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የኦሮሚኛ እና የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ዲ/ን ዮሴፍ ከተማ ከትላንት በስቲያ ለእስር መዳረጉን ተቋሙ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታውቋል።
ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 አካባቢ በሥራ ጉዳይ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ መካኒሳ አካባቢ ለጥያቄ እንፈልግሃለን የሚሉ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አፍነው ወስደውታል ሲል የሚዲያ ተቋሙ ገልጿል።
የኦሮሚኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ዲ/ን ዮሴፍ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተደጋጋሚ ቃለ ምልልሶች በማድረግ ወደ ምእመናን ያደርስ እንደነበር ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ተከትሎ በርካታ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች እና ምዕመናን እየታሰሩ መሆኑን በርካታ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛል፡፡ ማክሰኞ እለትም የማኅበረ ቅዱሳን ጭሮ ማዕከል አገልጋይ የሆነው ዶ/ር እንደሻው ዘርፉ በጸጥታ ኃይሎች መታሠሩ ተገለጧል።
በተጨማሪም መምህር ዐቢይ መኮንን፣ መምህር ምሕረተአብ አሰፋ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪ ፌቨን ዘሪሁን እና ዋና ጸሐፊ ብሩክታዊት እንዲሁም የማንቂያ ደውል አገልጋዮች ዲ/ን አማኑኤል አያሌው ፣ ዲ/ን ኪሩቤል አሰፋ እና ሌሎች በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በእስር ላይ ይገኛሉ።
የሰሞኑን ውጥረት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና መንግስት መካከል በተደረገው ውይይት መንግስት የታሰሩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና ምዕመናን ለመፍታት ፍቃደኛ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብረሃም በሰጡት ቃለ መጠይቅ አየተከናወነ ያለውን እስር በተመለከት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እያቀረብን ነው ብለዋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ እና መንግስት መካከል ተባብሶ የነበረው ውጥረት ተከትሎ ከየካቲት 2 ቀን ጀምሮ ዝግ የተደረገው የኢንተርኔት አገልግሎት እስካሁን ሳይከፈት ሰንብቷል፡፡አስ