ዜና፡ የፊልም አዘጋጁ እና የጉማ አዋርድ መስራች ዮናስ ብርሃነ መዋ ከሶስት ቀናት እስር በኃላ ተፈታ

ዮናስ ብርሃነ መዋ እና የቴሌቭዥን ፕሮግራም አቅራቢ ፍላጎት አብረሃም

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አባባ፣ ሰኔ 5/2015 ዓ.ም፡- የፊልም አዘጋጅ እና የጉማ ፊልም አዋርድ መስራች ዮናስ ብርሃነ መዋ ከሶስት ቀናት እስር በኃላ መፈታቱን አባቱ አቶ ብርሃነ መዋ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

በርካታ ፊልሞችን በማዘጀት የሚታወቀው የኪነ ጥበብ ሰው ዮናስ ብርሃነ ለዘጠነኛ ጊዜ በእስካይ ላይት ሆቴል አርብ ሰኔ 2 የተካሄደው የጉማ አዋርድ መሀርሃ-ግብር እንደተጠናቀቀ በፀጥታ ካላት በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል፡፡ አቶ ብርሃነ መዋ፣ የዮናስ እስር ይህ ነው የሚባል ምክኒያት የለውም ሲሉ ገልፀው ዛሬ ጠዋት ላይ ወደ ቤተሰቡ ተቀላቅሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ብርሃነ መዋ ስለልጃቸው እስር ሁኔታ በፌስቡክ ገፃቸው “እርብ ሰኔ 2 ቀን ከምሽቱ 5፡30 ሰአት የጉማ ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ ሌሊቱ 6፡00 ሰአት ዮናስና ባለቤቱ ሳምራዊት(ሊሊ) በፀጥታ አካላት ወደ ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተወሰዱ፣ ከለሊቱ 6፡00 ሰአት ባለቤቱ ስትለቀቅ ዮናስን ሳይለቁት ቀሩ፡፡ ቅዳሜ ሰኔ 3 ቀን ፍርድ ቤት ቀርቦ በ 5ሽህ ብር ዋስትና እንዲፍታ ቢወሰንም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በተለምዶ 3ኛ ተብሎ ወደ የሚጠራው ቦታ ተወስዶ ሰኞ ጠዋት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተነገርን” በማለት አስፍረዋል።

ዮናስ ትላንት በዛሬው እለት ሰኔ 5 ቀን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተለቆ ወደ ቤቱ ገብቷል ሲሉ አባቱ አቶ ብርሃነ መዋ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል፡፡  

ሰኔ 2 ቀን በተከናወነው ፕሮግራም ላይ ከታደሙት መካከል የቴሌቭዥን ፕሮግራም አቅራቢዋ ፍላጎት አብረሃም “ግንበሯ በጥይት የቆሰለ፣አፏ የተሰፋ” የሚመስል የገፅ ቅብ በፊቷ ላይ ተሰርታ የተነሳችው ፎቶ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት ሲሰራጭ ተስተውሏል፡፡

በምርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙ ስሙ እንዲጠቀስ ያለፈለገ እንድ ታዳሚ፣ ወደ 6 ሰዓት አካባቢ ዮናስ እና ባለቤቱ ቁጥራቸው አራት የሚሆኑ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ይዟቸው ሲወጡ እንደተመለከተ ገልጧል፡፡ በእለቱ በማህበራዊ ሚዲያ ፎቶዋ ሲሰራጭ የታየችው ግለሰብ ከ 3 ሰዓት በኋላ በስፍራው እንዳልታየች የገለፀው ታዳሚው፣ ምናልባት በእሷ ምክኒያት ወይም በመድረኩ ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር ሲደረግ ስለነበር ይመስለኛል ዮናስ በቁጥጥር ሰር ሊውል የቻለው ሲል ግምቱን ገልጧል፡፡

ሌላ የፕሮግራሙ ላይ የታደመው አንድ እውቅ ተዋናይ ምርሃ-ግብሩ አልቆ ስንወጣ ውጭ ላይ የፀጥታ ካላት ታዳሚዎችን እያስቆሙ ከስልካቸው አጥፉ ሲሉ ነበር በማለት ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፤ በሌላ አርቲስት የስነ ጥበብ ተቃውሞ የተነሳ ዮናስ ብርሃነ መዋን ማሰር እና በዋስ የመፈታት መብት መከልከል ሕግን የጣሰ እና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ የፊልም አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቅ በትዊተር እና ፌስቡክ ድረ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ጠይቀዋል፡፡

ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ በመደማቅ አከባበር የተካሄደው ጉማ አዋርድ በበርካታ ዘርፎች ለሙያተኞች ሽልማት አበርክቷል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.