ዜና፡ የኢትዮጵያ ጦርነት ከ1984 ጀምሮ በዓለም ላይ ከተካሄዱ ጦርነቶች ከፍተኛ ሞት የተመዘገበበት ነው ሲል አንድ ጥናት ገለፀ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የወደመ ታንክ (ፎቶ፡ ሮይተርስ/ቲክሳ ነገሪ)

አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 13/2015 ዓ.ም፡- ለትርፍ ያልተቋቋመው ኦስሎ የሰላም ጥናትና ምርምር ተቋም ባወጣው አዲስ ሪፖርት የኢትዮጵያ ጦርነት ከ1984 ጀምሮ በዓለም ላይ ከተካሄዱ ጦርነቶች ከፍተኛ ሞት የተመዘገበበት መሆኑን በመግለፅ በጦርነቱም ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል፡፡

ሀሙስ ሓምሌ 6  የወጣው ሪፖርቱ በ2022 በመንግስታት ጦርነት የተነሳ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ204,000 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ እና በዩክሬን የተደረጉት ጦርነት 89 በመቶውን ይይዛሉ ብሏል።

“የዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ትኩረት ቢያገኝም፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የነበረው ጦርነት በርካታ ህይወት የጠፋበት ነበር። የኡፕሳላ ግጭት መረጃ ፕሮግራም (UCDP) በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ወደ 81,500 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በተደረገው ጦርነት ደግሞ 100,200 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል” ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የጦር ወንጀሎችን እና ከጦርነት ጋር ተያያዘዥነት ያላቸውን ሞት መጠንን መመዝገብ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሞ “የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

ጦርነት በተካሄደባቸው ሁለቱ አመታት አጠቃላይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህወሓት በይፋ ባይገልፁም ነገር ግን በጥር ወር ላይ፣ የጦርነቱ ዋና አደራዳሪ የነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ በጦርነቱ እስከ 600,000 የሚደርሱ ሰዎችን ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተናግሯል።

ተቋሙ በ2022 አስር ዝርዝሮች ውስጥ ከተካተቱና በከፍተኛ ደረጃ በመባባስ ላይ ካሉ ሰባት ግጭቶች አንዱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የተደረገው ሌላው ጦርነት እንደሆነም አክሎ ገልጿል።

በ2022 ከተመዘገቡ 55 ግጭቶች ውስጥ ኢትዮጵያና ዩክሬንን ጨምሮ በስምንቱ ከ1,000 በላይ ሞት በመመዝገቡ በጦርነት ምድብ ውስጥ ተካተዋል ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.