ዜና፡”ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን እህትማማችነት እና ወንድማማችነት የበለጠ ለማጎልበት አጠናክረን እንቀጥላለን” – ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12/2015 .:- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ “ከሁሉም አጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እህትማማችነትና ወንድማማችነትን የበለጠ ለማጎልበት አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ ገለፁ፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ ይህን ያሉት የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ሲሆን ሰላማዊ ሂደትን ለማጠናከር የተጀመረውን የአመራር ለአመራር ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልፀው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኃላ በሙሉ አቅም ወደ ልማት በመግባት ድህነትን ለመቀነስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በልማትም ይሁን በጸጥታው ዘርፍ ወሳኝ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት ዶ/ር ይልቃል የክልሉ ሕዝብ የራሱን እና የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት ለማስከበር ከመንግሥት እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን ተሰልፎ ሲሠራ መቆየቱ ገልፀዋል፡፡

የክልሉን አስፈጻሚ አካላት እቅድ አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት በምክር ቤቱ ጉባዔ ባቀረቡበቅ ወቅት በአንድ በኩል ልማታችን እንዳይስተጓጎል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም እጦት የፈጠረውን ተግዳሮት ለመቋቋም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት። “በአስቸጋሪ ኹኔታዎች ውስጥ ኾነንም የተሻለ የልማት እና የኢኮኖሚ ለውጥ አስመዝግበናል” ሲሉም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሀገር በርካታ ተግዳሮቶች በመግጠማቸው ሰላማችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ልማታችን እና የማኅበረሰባችን ሕይወት በእጅጉ የተፈተነበት ወቅት ነውም ብለዋል። የውስጥ አንድነት እና ሰላማችንን ለማጠናከር ሁላችንም ከተረባረብን በቀጣይ ዓመታት የክልሉ ኢኮኖሚ የበለጠ እና ተጨባጭ እድገት ያስመዘግባል ሲሉም ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ “የክልሉ ሕዝብ የመጀመሪያ ጥያቄ ልማት እና የሕግ የበላይነት መከበር ነው” ሲሉ ገልጸዋል። መንግሥት የመሪነቱን ተግባር በትክክል በመወጣት የሕዝቡን ጥያቄ ፈጥኖ መመለስ አለበት ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመኾኑ መላ የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላሙን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተያዙ የልማት ሥራዎች አፈጻጸም የሚያበረታታ ነበር ያሉት አፈ ጉባዔዋ የማዳበሪያ እጥረት የወለደው የሕገወጦች መበራከት በክልሉ አርሶ አደሮች በኩል ቅሬታን የፈጠረ መኾኑን የገለጹት አፈ ጉባዔዋ ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.