ዜና፡ ኤርትራ ከትግራይ መሬቶች ለቃ እንድትወጣ አምባሳደሩ መጠየቃቸውን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት በአስመራ የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚን ጠርቶ ማነጋገሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5/2015 ዓ.ም፡- የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዳይሬክተር ጀነራል በአስመራ የብሪታንያ ልዑክን ጠርቶ ማነጋገሩን የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል በማህበራዊ ሚዲያ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

በአስመራ የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚ የተጠሩት ኤርትራ በሀይል ከያዘቻቸው የትግራይ መሬቶች ለቃ እንድትወጣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር በመቀሌ ባካሄዱት ጉብኝት መጠየቃቸውን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት በአምባሳደሩ ያልተገባ ንግግር ዙሪያ ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጠንከር ያለ መልዕክቱን ለማስተላለፍ በሚል መሆኑን አቶ የማነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር የሆኑት ዳረን ዌልች ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ምድር በተለይም በጉልበት ከያዘቻቸው የትግራይ አከባቢዎች እንድታስወጣ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አምባሳደር ዳረን ዌልች ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የፕሪቶርያው ስምምነት በግልጽ እንዳስቀመጠው ኤርትራ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ በተለይም ከትግራይ እንድታስወጣ ይጠይቃል፤ ይህም እንዲሆን እንግሊዝ ትፈልጋለች ማለታቸውም በዘገባችን ተካቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይባህር አከባቢ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሳራህ ሞንትጎምሪ እና ሉዑካቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን በማህበራዊ ሚዲያ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። ከልዑካኑ ጋር በዩናይትድ ኪንግደም የቀጠናው ሰብአዊ ረድኤት ዙሪያ፣ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር እና ተግዳሮቶቹ እና ሰላሙን ለማጽናት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት በትብብር መስራት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ መነጋገራቸውን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። ልዑካኑ በተጨማሪም ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ቦታ ድረስ በአካል በመሄድ ያለባቸውን ችግር መመልከታቸውን በመልዕክታቸው አካተዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.