ዜና፡ ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር የሆኑት ዳረን ዌልች ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ምድር በተለይም በጉልበት ከያዘቻቸው የትግራይ አከባቢዎች እንድታስወጣ መጠየቃቸው ተገለጸ። አምባሳደር ዳረን ዌልች ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንድስታወቁት የፕሪቶርያው ስምምነት በግልጽ እንዳስቀመጠው ኤርትራ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ በተለይም ከትግራይ እንድታስወጣ ይጠይቃል፤ ይህም እንዲሆን እንግሊዝ ትፈልጋለች ብለዋል። የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸምን ሀገራቸው እየተከታተለችው እንደምትገኝ መናገራቸውንም ዘገባው አመላክቷል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት የፕሪቶርያውን ስምምነት ተከትሎ አፈጻጸሙን የሚከታተለውን የአፍሪካ ህብረት የክትትል፣ ማረጋገጥ እና የተልዕኮ የማስከበር ቡድንን ለማገዝ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማስታወቁን ዘገባው አካቷል።

የብሪታኒያ መንግስት ልዑክ በትግራይ ጉብኝት እያካሄደ መሆኑን እና ከክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር መገናኘታቸውን ያስታወቀው ዘገባው የኤርትራ መንግስት በፕሪቶርያው ስምምነት ትግበራ ላይ እንቅፋት በመሆን ላይ እንደሚገኝ አቶ ጌታቸው ለልዑካኑ መግለጻቸውን እና የብሪታኒያ መንግስት ለፕሪቶርያው ስምምነት ትግበራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መጠየቃቸውን ዘገባው አካቷል።

በተያያዘ ዜና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይባህር አከባቢ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሳራህ ሞንትጎምሪ እና ሉዑካቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን በማህበራዊ ሚዲያ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። ከልዑካኑ ጋር በዩናይትድ ኪንግደም የቀጠናው ሰብአዊ ረድኤት ዙሪያ፣ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር እና ተግዳሮቶቹ እና ሰላሙን ለማጽናት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት በትብብር መስራት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ መነጋገራቸውን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።

ልዑካኑ በተጨማሪም ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ቦታ ድረስ በአካል በመሄድ ያለባቸውን ችግር መመልከታቸውን በመልዕክታቸው አካተዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.