ዜና፡ በፋኖ ታጣቂ ሀይሎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ የምስራቅ ወላጋና የሆሮ ጉዱሩ ነዋሪዎች ለረሃብ፣ ለበሽታና ለተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ መጋለጣቸውን ገለፁ

በምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃይ ፤ ፎቶ – ICRC

በጌታሁን ለገሰ @Birmaduu2

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28/2015 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል የሆሮ ጉዱሩና የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች በፋኖ ታጣቂ ሀይሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለሰብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አፋን ኦሮሞ ተናገሩ፡፡ ተፈናቃዮቹ ምንም አይነት ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ገልፀው ለደህንነት ስጋት፣ ለረሃብ፣ ለመኖሪያ ቤትና ህክምና እጦት መጋለጣቸውን ገልፀዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ከሆሮ ጉዱሩ ዞን አሙሩ ወረዳ ከሲደን ባርክሌቲ ቀበሌ ተፈናቅሎ ወደ ጊዳ አያና ወረዳ መሸሻቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለፁ አንድ አርሶ አደር፣ ሲኖሩበት በነበረው ቀበሌ በተፈፀመ ጥቃት ባለቤታቸው እና አንድ ልጃቸው እንደተገሉባቸው ተናግረዋል፡፡

“ታጣቂዎቹ ሰኔ 3፣ 2015 በከፈቱት ጥቃት በሲደን ባርክሌቲ ቀበሌ ልጄን እና ባለቤቴን በጥይት ተኩሰው ገድለውብኛል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው ከቀየው ተነፈናቅሎ በሌላ ቀበሌ የሚገኘው አርሶ አደር፣ ያሉበት ችግር ከባድ እንደሆነ ገልፆ “ በከተማ ውስጥ አየተዟዟርኩ ለምኜ የማገኘውን ነው የምመገበው” ሲል ተናግሯል፡፡ ተፈናቃዩ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ አካል ያደረገላቸው ድጋፍ አለመኖሩን  ገልጧል፡፡

ታጣቂዎቹ ከአማራ ክልል በመምጣት ከብቶች እና ሌሎች ንብረቶችን እንደሚዘርፉ እንዲሁም መኖሪያ ቤቱ እንደተቃጠለበት ተናግሯል፡፡ እንደ ነዋሪው ገለፃ ከሆነ በወረዳው ስር ካሉ ሶስት ቀበሌዎች ውጭ በሁሉም ቀበሎዎች ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የቡቴ ጉዲና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳባ “ከባድ ችግር ውስጥ ነን” ሲሉ ገልፀው “ወደ ቀበሌያችን ተመልሰን እርሻችንን እንዳናከናውን እዛ ያለው ሁኔታ አስፈሪ ሆኗል” ብለዋል፡፡ የአማራ ፅንፈኞች ቤታችንና እህላችንን አቃጥለውብናል በማለት ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዳባ 11 የቤተሰባቸውን አባላት ይዘው በጊዳ አያና ከተማ እየኖሩ መሆኑን ገልፀው መንግስት ለአንድ ቤተሰብ እያደረገ ያለው እርዳታ ለአንድ ሰውም የሚበቃ አይደለም ብለዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ከአንድ ቤት እየሞቱ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡

ግለሰቡ በጊዳ አያና ከተማ ውስጥ በልመኛ ላይ መሰማራታቸውን ገልፀው መንግስት የአማራ ታጣቂዎችን ከቀበሌዎቻችን ካላስወጣ በስተቀር አርሶአደሩ ሰላም መግኘት አልቻለም ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ መስተባበሪያ ጽ/ቤት ባወጣው ሪፖርት በወለጋ በሚገኙ አራቱ ዞኖች የፀጥታ ችግር መኖሩን በመግለፅ የሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ድጋፍ ለማድረስ መቸገሩን አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ በክረምቱ ዝናብ እና የውሃ ኩሬ (ማቆር) በመፈጠሩ የወባ በሽታ በመስፋፋት ላይ መሆኑን ገልጧል፡፡ እስካሁንም በመስራቅ ፣ ምዕራብ ቄለም ወለጋ ወረዳዎች 272,400 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በፀጥታ ችግር ምክንያት በምእራብ፣ ምስራቅ ሆሮ ጉዱሩ እና ቄሌም የሚገኙ 63 በመቶ የሚሆኑ የጤኛ ጣቢያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ አለመሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

በአማራ ታጣቂዎች ሰኔ 16 2023 ድንበር በማቋረጥ ወደ ሆሮ ጉዱሩ እና መስራቅ ወለጋ በመግባት ባደረሱት ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውንና 13 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ15 ሰዎች በላይ የት እንደገቡ እንደማይታወቅ አዲሰ ሰታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.