ዜና፡ ምክር ቤቱ “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል ስያሜ 12ኛ ክልል እንዲደራጅ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28 / 2015 ዓ.ም፡- የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል ስያሜ አዲስ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዲዮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ ዞኖችና ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ ኧሌና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል ክልል ስር እንዲደራጉ ውስኗል፡፡

ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የ6 ዞኖች (የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች) እና የ5 ልዩ ወረዳዎች(የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ) በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ መድረጉን ተከትሎ ነው፡፡

አፈ ጉባኤ  አቶ አገኘሁ ተሻገር የውሳኔ ሀሳቡ እንዲጸድቅ አቅርበው በሙሉ ድምጽ ደግፎ ማፅደቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታውቋል።

ቀድሞ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ውስጥ የነበሩ የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታ ጠምበሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ  ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚቀጥሉ ይሆናል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.