ዜና፡ በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ብቸኛው ሆስፒታል በጎርፍ በመጥለቅለቁ ታካሚዎች ለከፋ እንግልት ተጋለጡ

ኝንኛንግ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል የደረሰበት የጎርፍ መጥለቅለቅ ፡፡ ፎቶ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖርተሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30/2015 ዓ.ም፡- በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ብቸኛ የሆነው ኝንኛንግ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በጎርፍ አደጋ ምክንያት በሆስፒታሉና በተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ በአሁን ሰዓት ተኝቶ ታካሚዎችም ሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች ከሆስፒታሉ ውጭ በሚገኝ ደረቃማ ስፍራ ላይ ሸራ በመዘርጋት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አስተወቀ፡፡

ሆስፒታሉ በደረሰበት የጎርፍ መጥለቅለቅ አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገረ እንደሚገኝ የገለፁት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ኒያል ቶት ለተኝቶ ታካሚዎች ፍራሽ፣ አንሶላና መሠል መገልገያዎች እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

በሆስፒታሉ የደረሰውን ጉዳት ለማቃለል MSF የተባለ ግበረሰናይ ድርጅት ግምታቸው 650ሺ ብር የሆኑ የተለያዩ መድሃኒቶችን ድጋፍ ማድረጉን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ የገለፁ ሲሆን የተደረገው ድጋፍ የነበውን የመድሃኒት አቅርቦት ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሚያቃልለውና ድርጅቱ ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች ለማድረግ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶች እያከናወነ እንደሚገኝ እክለው ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ የተለያዩ ጥገናዎች ስለምያስፈልገው የክልሉ መንግስትም ሆነ ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል በ8 ወረዳዎች በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የተነሳ ከ74 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አዲስ ስታንዳርደ ዘግባለች

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጆር ወረዳ ኡንጎጊ ከተማ በመገኘት የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን በጉብኝታቸውም ወቅት “ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል” ማለታቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ ነሀሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ40ሺ በላይ የሚሆኑ አባዎራና እማዎራ ከመኖሪያ ቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን በጎርፉ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በዋንቱዋ፣ በመኮይ፣ በባዜል ቀበሌ፣ በፒሏል፣ በቢልጃኮክ እንዲሁም በላሬ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆሩ አባወራና እማወራ ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን እንዳሉት በሃገሪቱ ደጋማዉ አካባቢ በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በላሬ፣ በመኮይ በዋንቱዋና በኢታንግ ልዩ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማስከተሉን ተናግረዋል።አቶ ጋትቤል አያይዘዉም የጎርፍ አደጋዉ በቤት ዉስጥ ያሉ ቁሳቁሶች እንዲሁም በቁም እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል። በጎርፍ አደጋዉ ከቤት ንብረታቸዉ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ጠቅሰዉ ይህንንም ከክልሉ መንግስትና ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በመነጋገር አፋጣኝ ድጋፍ የሚደርስበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

በጎርፍ አደጋዉ ከመኖሪያ ቀዬአቸዉ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች  የጎርፍ አደጋዉ ድንገት የተከሰተ በመሆኑ ንብረቶቻቸውን ለማሸሽ እንኳን ጊዜ እንዳልነበራቸዉ እና  አደጋዉ ሲከሰት ልጆቻቸዉን ብቻ ይዘዉ ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ማረፋቸን ጠቅሰዉ መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸዉም መጠየቃቸው ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.