ዜና፡ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ሶስት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል፤ የፌዴራል ኃይሎች “ሸኔን ተባብራችኋል” በሚል ጥርጣሬ ስምንት ሰዎችን ገድለዋል፡ ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2014 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ በጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋናነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ በተፈጸመ ጥቃት አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነሾፌሩ፣ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ፡፡

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ “ከሸኔ ጋር ተባብራችኋል” በሚል ጥርጣሬ ስምንት ወጣቶችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በፌዴራል ጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ያለው ጥቃቱን ተከትሎ ከጥር 25 – 27 ቀን 2015 ዓ.ም ያደረገውን ምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ ባደረገበት ሪፖርት ሲሆን ጥቃቱ ዋና ኢላማውን ከጎቡ ሰዮ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ ያደረገ ስለሞኑን ገልጧል፡፡

ከሟቾቹ መካከል 42 ተጎጂዎች በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች ነበሩ ያለው የኮሚስኑ ሪፖርት አራት ሴቶች እና ሦስት ሕፃናት ከሟቾች መካከል መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 8 ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

ጥቃቱን ያደረሱት በርካታ ቁጥር ያላቸው የወታደር ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልፀዋል ያለው የኢሰመኮ ሪፖርት ታጣቂዎች ከጥር 25 ቀን በሦስት አቅጣጫ ወደ አኖ ከተማ በመግባት በግለሰቦች የንግድ መደብሮች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አኖ ቅርንጫፍ እና በሌሎች ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት ፈፅመዋል ብሏል፡፡ 

የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል በሰጡት ምላሽ ጥቃቱን መፈጸማቸውን አምነው፤ ነገር ግን ማስረጃ ሳያቀርቡ ጥቃቱ የተፈጸመው በካምፕ ውስጥ በስልጠና ላይ በነበሩ የአማራ ኃይሎች ላይ እንጂ ሲቪል ሰዎች ላይ አይደለም ማለታቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ 11 ቀበሌዎች እና ከሁለት የአዋሳኝ ወረዳ ቀበሌዎች በድምሩ ከ13 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአኖ ከተማ በመጠለያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያ ውጭ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ቁጥራቸው 10,800 የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በከተማው የነበረ ውስን የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጥቃቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም ታጣቂዎቹ በቦታው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አንፃር በቁጥር እጅግ በርካታ በመሆናቸው እና ጥቃቱ በዕቅድና ዝግጅት የተፈጸመ በመሆኑ ምክንያት ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ከነቀምቴ እስከመጣበት እስከ እኩለ ቀን 6፡00 ሰዓት ድረስ ታጣቂዎቹ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ግድያ እና ዘረፋ ፈጽመዋል ሲል ሪፖርቱ አስነብቧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት በተለያዩ መንገዶች ለጥቃት የተጋለጡ ሲቪል ሰዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለረጅም ጊዜ በግጭቱ ላይ እያደረገ ያለው የክትትል እና ምርመራ ግኝቶች ያሳያሉ” ብለዋል። አክለውም በተለይም በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉባቸው ቦታዎችን የጥቃት ኢላማ ማድረግ በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን የሚፃረር ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሁሉም ወገኖች ሲቪል ሰዎችን እና የሲቪል ሰዎችን ንብረት የጥቃት ኢላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ለተፈጸሙ ጥቃቶችም መንግሥት የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ አሳስቧል፡፡ አክሎም መንግሥት የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ ከመወጣት በተጨማሪ በክልሉ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለግጭቱ በአስቸኳይ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.